የሰንበት ት/ቤት

መግቢያ

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመሥራቿ በእግዚአብሔር ከተመሠረተች ጀምሮ ልጆቿን በተለያየ መንገድ ሰብስባ ከማስተማሯም በላይ ልጆቿ ያስተማረቻቸውን በተግባር እንዲፈጽሙ ስታደርግ ቆይታለች። ስታስተምርም ከመሥራቿ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕይወትን መሠረት በማድረግ ነው። ቀድሞ በዘመነ ኦሪት፣ ከዚያም በዘመነ ነቢያትና ነገሥት በኋላም በዘመነ ሐዲስ ልጆቿ እግዚአብሔርን እንዲያውቁና ርሱን በማክበር እየታዘዙ እንዲኖሩ አድርጋለች።
ቤተክርስቲያን ኵላዊትና ዓለም ዐቀፋዊት እንደመኾኗ መጠን አንዲት ናትና በየትኛውም ዓለም ያሉ የሰው ልጆች ኹሉ በየሚግባቡበት ቋንቋ እግዚአብሔርን ዐውቀው እንዲያመልኩት ሳታስተምር የኖረችበት ጊዜ የለም፤ ይኹን እንጂ ዓለሙ የርሷን ድምጽ አልሰማ ብሎ ከእግዚአብሔር ይልቅ በዲያብሎስ ክፉ ምኞት እየተመራ አእምሮውን አጥቶ እያበደ ይገኛል፤ የቤተክርስቲያንን ድምጽ የሰሙ ግን በእግዚአብሔር መዳፍ ተደግፈው በኅሊና ዕረፍት በደስታ ይኖራሉ፤ እየኖሩም ነው። ታዲያ ለዚኽ ኹሉ ጉዞዋ ልጆቿ ተባብረው በፈጣሪዋ በእግዚአብሔር ረድኤት ዛሬ ላይ ደርሳለች፤ ቤተክርስቲያን ዓለም ዐቀፋዊት እንደመኾኗ ስለ ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴ መጻፍም ኾነ መናገር የጊዜ ጉዳይ ኾኖ ስለሚገድበን ስለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ትንሽ እንጠቁምዎ!
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፥ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብለው ከሚያምኑ ከሕንድ፣ አርመን፣ ሶርያና ግብጽ አኀት ተብለው ከሚጠሩት አንዷ ናት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታዲያ በመግቢያችን እንደገለጽነው ልጆቿን ሰብስባ እያስተማረች ወደ መንግሥተ እግዚአብሔርም እንዲገቡ በተግባር እንዲፈጽሙ ማለትም በሥጋ ወደሙ እየታተሙ በጎ እገዛንም ለፍጥረት ኹሉ እንዲያደርጉ እያስደረገች ሲኾን በኢትዮጵያ በኹሉም ክልሎችና አካባቢዎች ልዩ ልዩ መዋቅሮችን በመዘርጋት አገልግሎቷን ለኹሉም ተደራሽ እያደረገች ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤት ትርጕም

ሰንበት የሚለው ቃል በእብራይስጡ “ማቆም፤ ሰርቶ ማረፍ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ እግዚአብሔር ስድስት ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን እንዳረፈ (ዘፍ2*2) እለተ ሰንበት በሥጋ አርፈን በመንፈስ የምንበረታበት (የዮሐ.ራዕይ 1*3) የእግዚአብሔርን ውለታ የምናስታውስበት (ዘጸ 20*10) መልካም በማድረግ የምንጠመድበት ዕለት ነው፡፡ (ማቴ 12*2)።
በዚኽ ዕለት የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበትና ውለታው የሚወሳበት ሥፍራ ሰንበት ት/ቤት ይባላል፡፡ በእረፍት ቀናቸው /በሰንበት/ መንፈሳዊ ትምህርት የሚማሩ በእግዚአብሔር ቤት እያደጉ ለዓለም ብርሃን የሚኾኑ የክርስቲያን ልጆች ደግሞ ሰንበት ተማሪዎች ይባላሉ፡፡

የሰንበት ት/ቤት ዓላማ

ሕፃናትን በምግባር ማሳደግ፤ ወጣቶችን በሃይማኖት ማጎልመስ እና የአባቶችን አደራ ተረክቦና ጠብቆ የሚያስረክብ ባለ ራዕይ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት ጥቅም

፩. ሰንበት ትምህርት ቤት ሃይማኖቱን ጠንቅቆ ያወቀ መልስ ያለው ትውልድ ይፈጥራል፡፡
፪. ለቤተ-ክርስቲያንና ለሃገር የውስጥ ጉልበት፤ የውጭ ውበት የሚኾኑ ምርጥ ዜጎችን ያሥገኛል፡፡
3. ለቤተ-ክርስቲያን ተልዕኮዋን የሚያሳኩ እጆች፤ ጠላቷን የሚረቱ ኃይሎች የሚኾኑ ባለ ራዕይ ወጣቶችን ይቀርጻል፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤት ክርስትናን በማስፋፋት ምንፍቅናን በመከላከል ዓለማ›ቀፋዊ እውቅና አለው፡፡ በሰንበት ት/ቤት ያደጉ ልጆች በሚሰማሩበት ሥፍራ የተሳካላቸውና በማኅበራዊ ሕይወት የተዋጣላቸው መሆናቸው ሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ መሆኗን ያረጋግጣል፡፡ ሰንበት ት/ቤት ሥራ አስለምዳና ጸባይ አርማ ወደ ስኬት ተራራ የምታወጣን ደግ እናትን ትመስላለች፡፡ አበው እንደሚሉት እሳት ያልነካው ሸክላና በሰንበት ት/ቤት ያልተማረ ወጣት አንድ ናቸው፡፡

የሰንበት ት/ቤት አመሠራረት

በብሉይ ኪዳን “ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም እረፉ” (ዘጸ 20*10) በተባለው አምላካዊ ቃል መሠረት የአይሁድ ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል በመስማትና ውለታውን በማሰብ ያከብሩት ነበር፡፡ በዓመትም ሦስት ጊዜ ልጆች ወደ አምልኮ ሥፍራ ይወሰዱ እንደነበር አሪት ዘጸአት 23*17 ያስረዳል፡፡ የነቢዩ ሳሙኤልን ታሪክ ስናስታውስ ደግሞ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ ያድጉ እንደነበር እንረዳለን፡፡ (1 ሳሙ.3*1)
በሐዲስ ኪዳን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው በመቅደሱ መገኘቱ የሃይማኖት ልጆቹ በእግዚአብሔር ፊት ማደግ እንዳለብን አብነት ነው፡፡ ሉቃ 2*46 በሚያስተምርበት ጊዜም ሕፃናትን ማቅረቡ (ሉቃ 18*16) ልጆቻችሁ በፊቴ ይመላለሳሉ፤ ከቤቴ በረከትን ጠግበው ተንኮል በሌለበት ቃሌ ይደጉ ማለቱ እንደኾነ እንረዳለን፡፡
የመጀመርያዎቹን ክርስቲያኖች ሕይወት ስንመለከት ልጆቻቸው አብረው ተጉዘው የክርስትናንም የፍቅር ማዕድ ተካፍለው የአባቶቻቸውንም ሃይማኖት ወርሰዋል፡፡ ክርስትናው እየሠፋ ሲሄድ መከራም እየበዛ ሲመጣ ልጆችን በክርስቲያናዊ ዓላማና በሰማያዊ ራዕይ ማሳደግ ስላስፈለገ በ 200 ዓ.ም ገደማ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤት ተመሠረተ፡፡
ዓለም አቀፋዊና ክርስቲያናዊ ከኾኑት የአንጾኪያና የእስክንድርያ ት/ቤቶች የሚወጡ ደቀ መዛሙርት ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር ተጠቃሾች እንደኾኑ ታሪክ ይናገራል፡፡
ሀቢብ ጊዮርጊስን የመሰሉ ግብፃዊያን ዲያቆናት ወጣቶችን በሰንበት ትምህርት ቤት በማሰልጠን የእስክንድርያን ቤተ-ክርስቲያን ከመናፍቃን አድነዋል÷ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የቤተ-ክርስቲያን የውስጥ ጉልበት፤ የውጭ ውበት በመኾን ዓላማዋን ያሳካሉና፡፡

ሰንበት ት/ቤት በኢትዮጵያ

ትውልዱ ወደ ዘመናዊ ትምህርት በማዘንበል ሃይማኖቱን ችላ እንዳይል በማሰብ አባቶቻችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን በማወቅ የሚያድግ፤ መልስ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ከ 1935-1940 ዓ/ም ባለው ጊዜ ሰንበት ት/ቤትን በአዲስ አበባ መሠረቱ፡፡ በጊዜውም “ተምሮ ማስተማር” በሚል መጠሪያ ይታወቅ ነበር፡፡ ቀጥሎም በ 1953 ዓ.ም መመሪያ ወጥቶለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ትእዛዝ በየአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያኑ ሰንበት ት/ቤት እንዲቋቋም የተደረገ ሲኾን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመን በቃለ ዓዋዲው የሰንበት ት/ቤት አወቃቀር መመሪያ ተካተተ፡፡