የልማት እንቅስቃሴዎች

የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት አንጋፋ ከሚባሉት ሀገረ ስብከቶች አንዱ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ዋግኸምራን ጨምሮ በእግር እና በበቅሎ እየተንቀሳቀሱ በርካታ መንፈሳዊና ቁሳዊ ልማት አስፋፍተዋል፡፡

  • በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን ታሳቢ ያደረጉ የእንግዶች ማረፊያ ሆቴሎች፣ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ለሚያገለግሉ ሊቃውንት ድጎማ የሚውል የገቢ ማስገኛ ሁለገብ ሕንፃ ወልድያ ከተማ ላይ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
  • አሁንም በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የልማት ሥራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መመሪያ ሰጭነትና በሀገረ ስብከቱ የገንዘብ ድጋፍ ጭምር ኹሉም ወረዳ ቤተ ክህነቶች የሚሰጡትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር በወረዳ ዋና ከተሞች የገቢ ማስገኛ ሕንፃዎችን ገንብተው ገቢ ማመንጨት ጀምረዋል፡፡
  • የአብነት ትምህርት ቤቶችን በዘመናዊ መንገድ በማደራጀት ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርታቸው እንዲያውሉ ታስቦ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሊቀ ጳጳስ ከመሆናቸው በፊት የጀመሩትና አሁን ደቀ መዛሙርትን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው የአስፋ ገነተ ጽጌ ፈለገ አእምሮ መንፈሳዊ ት/ቤትና 300 ወንዶችና 100 ሶቶችን ተቀብሎ ለማስተማር ታስቦ የሚገነባው የወልድያ ምሥራቀ ፀሐይ ወይብላ ቅድስት ማርያም አዳሪ መንፈሳዊ ት/ቤት ይገኙበታል፡፡
  • በሀገረ ስብከቱ የ10 ዓመት መሪ እቅድ መሠረት በሀገረ ስብከቱ አስራ አራቱም ወረዳዎች አንድአንድ በዘመናዊ መንገድ የተደራጁ የአብነት ት/ቤት እንዲገነቡ የቦታ ርክክብና የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነስርዓት ተካሂዷል፡፡
    በዘመናዊ ትምህርት ትውልዱን አንጾና ቀርፆ ለማሳደግ ሀገረ ስብከቱ አንድ አጸደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ያለው ሲሆን በአድባራትም በርካታ ት/ቤቶች እየተከፈቱ ነው፡፡