ዐይንና ጆሮ የሚያሻው፣ የቅዱሱ ዐይንና ጆሮ (ክፍል ኹለት)

ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ/ም (የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ)

በክፍል አንድ ዳሰሳችን ዐብነት ትምህርት ቤቶቻችንን ስለማሻሻል አስፈላጊነትና ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ወደ ሲመተ ጵጵስና ከመምጣታቸው በፊት የጀመሩትን በወፍ በረር መዳሰሳችን ይታወሳል። ክፍል ኹለትን ደግሞ እንደሚከተለው እናስቃኛችኋለን።

አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤቶች በዘመናዊ አደረጃጀት የሚስፋፉት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ህልውና የሚኖሩ ግልገሎችን የሚያሰማሩ፣ ጠቦቶችን የሚጠብቁ፣ በጎችን የሚያሰማሩ ተተኪ ካህናትን ለማፍራት ነው። “በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተተኩልሽ (መዝ ፵፭፥፲፮) እንዲል። ውስብስቡን ዓለም ተሻግረው የሚያሻግሩ ዘመኑን የሚዋጁ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን ከልጅነት ዕድሜ ጀምሮ እየኮተኮቱ ማሳደግ፣ ማሠልጠንና ማፍራት ያስገደደውም ለዚህ ነው።

እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ዘመኑን መዋጀት ሲባል በሥነ-ምግባር የታነጸ ድርሻና ኀላፊነቱን የሚወጣ፤ ትውልድንና ሀገርን መታደግ የሚችል የሃይማኖት አባት ማፍራት ነው። ካህን እንደ ቅዱስ ያሬድ በስብሐተ ማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው፥ እንደ ሐዋርያት ደግሞ በዐውደ ምሕረት አገልግሎቱ ሙሉ መኾን ይጠበቅበታል።

ካህን ባራኪና አመስጋኝ ነው። ካህን አስታራቂ፣ መሪ፣ ንጉሥ፤ ቁሳዊ ብቻ ሳይኾን ሰብአዊ መሐንዲስ፤ ተመራማሪ ነው፤ ከፍ ሲልም ካህን ቅዱስ ነው። እነ ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና ሌሎች ቅዱሳን አባቶቻችን አብነቶቻችን ናቸው። አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤቶቹ የቅዱሳኑን ፈለግ የሚከተሉ፣ በቃልና በሕይወት ክርስትናን የሚኖሩ የተሟላ ሰብእና ያላቸው ሰዎችን ለመፍጠርና ለመተካት ነው እየተገነቡ ያሉት።

ንጉሡና ካህኑ ቅዱስ ላሊበላ ያኔ የታየው ታሪክ ማስቀመጡ አልነበረም፤ ቅርስ ማውረሱም አልነበረም። ይልቁኑም የንጉሡ ዐይንና ጆሮ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ተአምራት የሠራባቸውን ቅዱሳት መካናት ለመሳለም የሚጓዘው የኢትዮጵያዊ ወገኑን የጉዞ እንግልት ማስቀረት ነበር።

እነሆ፥ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስም በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወታቸው እየተቸገሩ የሔዱበትን አስቸጋሪ ጉዞ በሌሎች እንዲደገም አለመፈለግ ብቻ አይደለም። ቀጣዩን ዘመን በዐይናቸው ዐዩት፤ በእዝነ ልቡናቸው አደመጡት። ቅዱስ ላሊበላ ለራሱ ምቾት ሳይኾን በጉዞ ላይ የሚደርስ የዜጎች እንግልትን መፍትሔ እንደሰጠ ኹሉ በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ቅድስት ቤተክርስቲያንን የሚያስቀጥሉ ተተኪ ሊቃውንት እንግልት ብፁዕነታቸውንም አሳሰባቸው። ሰሜን ወሎ ላይ ተቀምጦ የዓለምን ጆሮና ዐይን ቀልብ የሳበው የቅዱስ ላሊበላ አሻራ ዘመናትን ተጉዞ በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ዐይንና ጆሮ ዳግም ታሪክ ሊሠራ መቄት ላይ አሐዱ ያለው በሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ክልኤቱ፣ ሠለስቱ … ማለት ጀምሯል።

ብቸኛው ዓለም ዐቀፉ መሐንድስ እንደ ዛሬው አማራጭ መጓጓዣ ሳይፈጠር ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን የጉዞ እንግልት ተረድቶ መፍትሔ እንዳስቀመጠው ኹሉ ብፁዕነታቸውም የቤተክርስቲያን አርቆ ዐሳቢ ልጆችን በማስተባበር ሀዲዱን ጠብቀው፣ መሪውን ጨብጠው መጓዙን ተያይዘውታል፡፡

የቅዱሱ አሻራ ከመንፈሳዊ ሀብትነቱ ባሻገር የኪነ-ሕንጻ ጥበቡ የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ በዓለም ቀዳሚ ከኾኑት መስሕቦች አንዱ እንደኾነው ኹሉ ሀገር የሚያሻግሩ ሊቃውንት የሚቀረጹባቸው የአብነት ትምህርት ቤት ፕሮጀክት ግንባታዎችንም ብፁዕነታቸው መሠረት መጣል ጀምረዋል። ፈለገ አእምሮ በወንድ ወይብላ ምሥራቀ ፀሐይ ደግሞ በኹለቱም ጾታ አድማሱን ማስፋት ቀጥሏል።

የወልድያ ወይብላ ምሥራቀ ፀሐይ ቅድስት ማርያም አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ፕሮጀክት “አልቦ አንስት ወአልቦ ተባዕት በኀበ እግዚአብሔር” የሚለውን ምስጢር ሊገልጽ ለየት ያለ ራእይ ሰንቋል። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአጠቃላይ ደቀመዛሙርት ፳፭ (25) በመቶ ሴቶች ደቀመዛሙርትን በአዳሪ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቱ ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ እየተሠራ ነው። ይህም በአንድ ጎኑ በመንፈሳዊ ዕውቀት ያልበሰሉትን ወገኖች በማሳሳት ወይም እውነት በማስመሰል ግራ በማጋባት “መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን ይጨቁናል” የሚል አመለካከት ላላቸው ወገኖች መልስ የሚሰጥ ትምህርት ቤት ነው።

ነቢይነት፣ ሰማዕትነት፣ ንጉሥነት፣ ጀግንነት፣ አሸናፊነት፣ ሩኅሩኅነትና ቅዱስነት፣ ሊቅነት፣ አስታራቂነት ለወንዶች ብቻ ሳይኾን ለሴቶችም የተሰጠ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል። ለአብነትም፡- ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ቅድስናን ተቀዳጅታለች። በሌላ መልኩ ደግሞ ሰውና ሰውን ከማስታረቅ ባለፈ በፊትም በኋላም ያልተሞከረን የሽምግልና ሥራ ሳጥናኤልንና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማስታረቅ መንፈሳዊ ኀላፊነቷን ተወጥታለች።

በቤተክርስቲያናችን ከጥንት እስከ ዛሬ እንደ ወንዶች ኹሉ ሴት ሊቃውንትም አሉ። እንደ ሙያ የድጓ መምህር፣ እንደ ሀገር መሪ የቴክኖሎጂና የዘመናዊነት ባለራእይ ንጉሥ ዐፄ ቴዎድሮስ፡- ይማሯል እንደ አካልዬ፤ ይዋጓል እንደ ገብርዬ።እያሉ የሚያደንቋቸው፤ ለቅድስት ቤተክርስቲያንና ለሀገር ህልውና ከኖሩት እንደ መምህር አካለወልድ ዓይነት ሊቃውንት ጎን በፍልስፍናው በቅኔው የሚራቀቁ ሴት ሊቃውንትም ነበሩ።

ለምሳሌ፡- በአማርኛ ቋንቋ ንጥረ ድምፅ ደረጃ (የፊደል ቅደም ተከተል) ፩ኛና ፴፪ኛ ላይ በሚገኙት ፊደላት ሰማይና ምድር ያልፋል። የሚለው የወንጌል ምስጢር አስመስሎ ሀለፈ ሰማዩ ብለው ጉት ቅኔ በመቀኘት ተራ ቅኔ አዋቂ ሊረዳው በማይችል አገላለጽ የምጡቅ ሐሳብ ባለቤት የኾኑት ሊቋ እሟሆይ ገላነሽ ተጠቃሽ ናቸው። ዛሬም ጉባኤ አስፍተው፣ ወንበር ዘርግተው የሚገኙ ሴት ሊቃውንት አሉ። ቅድስት ቤተክርስቲያን ምንጯ አልደረቀምና።

በኹለቱም ጾታዎች ኹለገብ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን ለማፍራትና ለመተካት፣ ከ23 ሄክታር በላይ በኾነ ቦታ ላይ አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው። የሙያና የጉልበት ዐሥራት አበርክቶን ጨምሮ በጎ አድራጊዎች በለገሡት ከ6 ሚሊዮን 678 ሺህ ብር በላይ በኾነ ወጭ የ7 ጉባኤ ቤቶች (መማሪያ ክፍሎች) ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።

ሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ቡራኬ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የወልድያ ወይብላ ምሥራቀ ፀሐይ ቅድስት ማርያም አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ፕሮጀክት 44 የደቀመዛሙርት መኝታ ክፍሎች፣ 18 መጸጃ ክፍሎች፣ 12 መታጠቢያ ክፍሎችና የተማሪዎች መኝታ አገልግሎት ክፍል ማስተባበሪያ ቢሮ ያለው ባለ ኹለት ወለል የወንዶች ደቀመዛሙርት መኖሪያ ሕንጻ ግንባታም አሁን ላይ 80 በመቶ ደርሷል። እስከ አሁን ባለው ግንባታም ከኻያ ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል።

የፕሮጀክት ግንባታው በሀገረ ሰብከቱ ዕቅድና ዐቅም ልክ ምእመናንን በማስተባበር በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚገነባ በመኾኑ ባለሙያ በመቅጠር ቤተክርስቲያን በምህንድስናው ዘርፍ ፋና ወጊ መሆኗን የሚያስመሰክር ሥራ በጥራት እየተሠራ ነው።

የግንባታ ማሽኖች ተሟልተው እየተሠራ ሲሆን ከ40 ሽህ በላይ ብሎኬቶችን በራስ ዐቅም በማምረት ጥቅም ላይ ማዋል ተችላል። ይህም ከቴክኖሎጂ ሽግግር በተጨማሪ ወጭ ቆጣቢ አሠራር ለመከተል ዕድል ከፍቷል።

ፕሮጀክቱ ያልተጠናቀቀውን የወንዶች ደቀመዛሙርት መኖሪያ ሕንጻ ጨምሮ G+2 የመመገቢያ አዳራሽ፤ G+0 የመምህራን መኖሪያ ሕንፃ፣ G+1 የሴት ደቀመዛሙርት መኖሪያ፣ G+2 የአስተዳደር ሕንፃ፣ G+0 የእንግዶች ማረፊያና G+0 የካህናት ማሠልጠኛ ሕንጻ በአጠቃላይ የተለያየ መጠንና ቅርጽ ያላቸውን 6 ሕንፃዎች ለመገንባት በወቅቱ የገበያ ኹኔታ ከአንድ መቶ ሚሊየን ኹለት መቶ ዐምስት ሺህ ብር በላይ ያስፈልጋል። እነዚኽ የምእመናንን የሐሳብ፣ የጉልበት፣ የገንዘብ ትብብርን የሚጠይቁ ከቀሪ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

የአስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈለገ አእምሮ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤትና የወልድያ ወይብላ ምሥራቀ ፀሐይ ቅድስት ማርያም አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን እስከ አሁን ለተከናወኑ ተግባራት ከመቶ ሠላሣ ኹለት ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎባቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ መጭውን ትውልድና የቤተክርስቲያኗን የነገ እጣ ፈንታ አርቆ በማየት በኹሉም ወረዳዎች የመንግሥት መዋቅራትን በማነጋገር ቦታ በመቀበል ሰው የሚሠራባቸውን የአብነት ትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ለምሳሌ፦ የታላቁ የቅኔ ሊቅ የዮሐንስ ገብላዊ መታሰቢያ የኔጃ ቅዱስ ሚካኤል ዋድላ ወረዳ ላይ፣ የሰባቱ ድድቅ መታሰቢያ የጨረቃ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቅኔ ጉባኤ ዳውንት ወረዳ ላይ በጊዜያዊ ማደሪያ ደቀመዛሙርት ተቀብለው በማስተማር ላይ ሲሆኑ የግንባታ መሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የአራቱ ጉባኤያት፣ የዋልድቢት ቅድስት ማርያም፣ የደብረ ሲና ራማ ቅድስት ኪዳነምሕረት፣ የሰዳቱ ደብረ መዊዕ አቡነ ተክለሃይማኖት የአንድነት ገዳም የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር እየተሠራ ነው፡፡

ሀገረ ስብከቱ እነዚኽን ታላላቅ ግንባታዎች ተግባራዊ ሲያደርግ ነገሮች አልጋ በአልጋ ኾነውለት አይደለም፤ መልካም ዕድሎችን እንደ ጸጋ፤ ፈተናዎችን ደግሞ በእግዚአብሔር ኀይል በመቋቋም እንጂ።

ፈተናዎችን ስንቃኝም ያለመከራ ጸጋ እንደማይገኝ ቢታወቅም ፈተናዎቹ በዕቅድ መሠረት ለማስኬድ አላስቻሉም። የፕሮጀክት እንቅስቃሴው በሰፊው ከተበሰረና ከተስተጋባ ጀምሮ የሰላም እጦት በመከሰቱ በማቴሪያል አቅርቦት፣ በገንዘብ አሰባሰብና በግንባታ ሒደቱ የፈጠረው ተፅዕኖም ሰፊ ነው።

የሰላም ዕጦቱና ወቅቱ የፈጠረው የዋጋ ንረት ያስከተለው የሕዝብ ጉስቁልና ቤተክርስቲያኗን በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ሲደግፉ የነበሩ ዛሬ ላይ ቁሳዊና የሥነ-ልቡና ድጋፍ ፈላጊ ኾነዋል። የተሻሉ ሰዎችን ለመፍጠር የተወጠነው ፕሮጀክት አስፈላጊ ቢሆንም የሰው መኖር ይቀድማልና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መሪነት ሀገረ ስብከቱ ወላጆቻቸውን በጦርነት ለተነጠቁ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኀላፊነትን ለመወጣት የተሰጠው ትኩረት በፕሮጀክት ፍጥነቱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ሀገረ ስብከቱ ፕሮጀክቶችን በራስ ዐቅም ለመገንባት አንዳንድ ከራስ ወዳድነት የሚመነጩ ለግል ጥቅም የዋለ በማስመሰል ቤተ ክርስቲያኗ በልማት እንዳትሰማራ እንቅፋት በመፍጠር በስም ማጥፋትና አድማ በማድረግ ምእመናን የሐሳብ፣ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ከማድረግ እንዲታቀቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የማደናገር ሥራ ለመሥራት ሲጣጣሩ ይስተዋላል።

ለመኾኑ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሰብአዊ ልማትን ከማስፋፋት ባሻገር ከልመና ወጥቶ በራስ የኢኮኖሚ ዐቅም አገልግሎትን ለማዳረስ በሀገረ ስብከቱ የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ እንዲኹም የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅድ ምንድን ነው? የሚለውን የዳሰሰ የመጨረሻውን ክፍል ይዘን እንቀርባለን።

ቸር እንሰንብት!