ዐይንና ጆሮ የሚያሻው፣ የቅዱሱ ዐይንና ጆሮ (ክፍል አንድ)

ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ/ም (የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ)

ጠቢቡ “ልጄ ሆይ ሰው ኹን!” (፩ነገ ፪፥፫) ሲል የሀገራችን ብልኁ አርሶ አደር ደግሞ ባልተማረ አንደበቱ፦
“ሰው ፡ ማለት ፥ ሰው ፡ መሆን፤
ሰው ፡ የታጣ ፡ ለታ ፥ እሱ ፡ ሰው ፡ የሚሆን።” በማለት የመጽሐፉን ሐሳብ በራሱ ዕውቀትና አመለካከት በሥነ-ጽሑፍ ስልት ይገልጸዋል።

የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በብዙ ነገር እድለኛና ባለጸጋ ነው። የእነ ቅዱስ ላሊበላ መንፈሳዊ ጸጋና የምሕንድስና ጥበብ ውጤት መገኛ ብቻ ሳይሆን፥ ምንጊዜም ጠቢባን ሰዎች ይወጡበታል፡፡ ሊቃውንትም ይፈልቁበታል፡፡

አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ አስቸጋሪው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳይበግራቸው የመንገድ መሠረተ ልማት የተሟላበትን በተሽከርካሪ፣ የመንገድ መሠረተ ልማት የሌለውን አካባቢ በባሕላዊ መጓጓዣ፣ ከፊሉን ደግሞ በእግር እየተጓዙ ሕዝባቸውን ባርከዋል፤ አስተምረዋል። አሁን ደግሞ “በቃኝ” በሚለው የሊቅነት ሚዛነ ሰብእናቸው በጸሎት ታግዘው ሰው ተክተዋል።

“ሀገረ ሰብከቴን ለማን ላስረክበው? ብየ እጨነቅ ነበር፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ሰማኝ፤ አሁን ደስ ብሎኛል ሁሉም ነገር ከጠበኩት በላይ እየሔደልኝ መሆኑን እያየሁ፣ እየተረዳሁ ነው” በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ – በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛ አባት ስለተኩ እግዚአብሔር ይመስገን ይህ ሁሉ የእርሱ ሥራ ነው ይላሉ። አባት እናቶቻችንም “ልጅ ከአባቱ ሲበልጥ ነው እንጂ ከአባቱ ጋር ዕኩል ከሆነ ቁና ዘርቶ ቁና ማምረት ነው” እንዲሉ የአቡነ ቄርሎስ ሐዋርያዊ ፈለግ በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በመጠንም በዓይነትም ሰፍቶና ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ቤተክህነት የያዘውን እምቅ መንፈሳዊ ጉልበትና ትኩረት የሚያሻውን፣ “የቅዱሱን ዐይንና ጆሮ” በሚል ያዘጋጀነውን አጭር ጽሑፍ እንደሚከተለው እናስቃኛችኋለን፤ መልካም ንባብ።

ጥንት ጀምሮ በጠበብት አባቶች፣ በዐራት ዓይና ሊቃውንት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚጠቅም ዘመን ተሻጋሪ አሻራ በሚያስቀምጡ አባቶች የታደለው የሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ቤተክህነት ዛሬም ለትውልድ የሚተላለፍ ችግር ፈች አሻራ ለማስቀመጥ የሚተጉ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተችረውታል፡፡

በአብነቱ ዘርፍ ያለውን ቁልፍ ችግር ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በዐይናቸው ማየትና በጆሯቸው ማዳመጥ ብቻ አይደለም – በሙሉ ሕይወታቸው ኖረውታል፤ ቀምሰውታል። እሾኽ እንቅፋቱን፣ አቀበት ቁልቁለቱን፣ እየተራቡ፣ እየታረዙ፣ ጥሬ ቆርጥሞ መማርን ኖረው አድገውበታል።

ይህን ችግር መቅረፍ ደግሞ አንዱ ተቀዳሚ ተግባራቸው በማድረግ፤ የአብነት ተማሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ውጣ ውረዱን ታግሰው ከውሻ ጋር እየተናነቁ የዕረፍት ጊዜ ሳይኖራቸው የሚያጠፉትን ጊዜ ለመቀነስ፣ ከልመና፣ ከመደበኛ ወንበር፣ ከማኅበር ቀለም፣ ከግል ቅጸላ፣ ከአገልግሎት፣ ከማኅበርና ከግል ጸሎት የምትተርፈውን ሽርፍራፊ ሰዓት በመቃብር ቤት፣ አልያም በደሳሳ ጎጆ ይገፉት የነበረውን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር የተሻለ መንገድ የማመቻቸቱን ሥራ ብፁዕነታቸው ያለዕረፍት እየሠሩ ነው።

በሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ሰብከት ቤተክህነት በመቄት ወረዳ ቤተክህነት የአስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈለገ አእምሮ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዛሬ ላይ ከ፸፭ (75) የማይበልጡ ደቀመዛሙርት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በቀጣይ የመቀበል አቅሙን ወደ ፭፻፴ (530) ከፍ ለማድረግ B+G+፯ የሕንጻ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

ስፋታቸው ከ፳፬ (24) አስከ ፷፰ (68) ካሬ ሜትር የኾኑ ፮ (6) ጉባኤ ቤቶች (የመማሪያ ክፍሎች) ተገንብተው፥ መቀመጫ ወንበር ተሰናድቶ፥ የድጓው ቅኝት፣ የዜማና ቅዳሴውን ቅላጼ፣ የመጻሕፍትን ምስጢር ማራቀቅ፣ የቅኔውን ግስ ማውረድ፣ በቅኔው አገባብና ዐይነ ውሃ መፈላሰፍ ከጀመሩ ፮ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በዚኹ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በአንድ ክፍል ዐሥር ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ዘጠኝ (፱) የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች፣ አልጋዎች፣ ፍራሽና ብርድልብስ፣ የመመገቢያና የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ቤተ-መጻሕፍት ተሟልቶላቸዋል። የተወሰኑ ደቀመዛሙርት በድጓ፣ በቅዳሴ ወደ ምስክር ት/ቤቶች የሔዱ ሲኾን፤ ቍጥራቸው ፲፩ የኾኑ ደቀመዛሙርት በሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በ፳፻፲፮ (2016) ዓ.ም ተመርቀው አልጫውን ዓለም ሊያጣፍጡ መንፈሳዊ ትጥቃቸውን ይዘው “ሒዱና አስተምሩ” ለሚለው ሐዋርያዊ ተልዕኮ ተሠማርተዋል። ይኽም የኾነው ደቀመዛሙርቱ ለምግብ፣ ለአልባሳት፣ ለንጽሕና መጠበቂያ ሳይጨነቁ በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተመቻችቶላቸው ነው።

ለእዚሁ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የገቢ ማስገኛ መሆን የጀመሩት የላም ርባታ፣ የወተት ማቀነባበሪያና የወፍጮ ቤት ፕሮጀክቶች ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል። ይኽም ቤተክርስቲያኗ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ባለፈ ማኅበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ስለመኾኑ ማሳያ ነው።

በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐሳብ አፍላቂነትና አስተባባሪነት እየተገነቡ ያሉ የአብነት ትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች አርቆ ላስተዋለ፣ ዓላማውን በውል ለተረዳ፣ ታሪክን ለሚጠይቅና ለሚያውቅ ከውጭ የተቀዳ (የተኮረጀ) ሳይኾን ንግሥናን ከቅድስና አስተባብረው ከያዙ ከእነ ቅዱስ ላሊበላ በተገኘ ተሞክሮ የሚታነጹ መንፈሳዊ የልህቀት ተቋማት ናቸው።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የሰውን ልጅ ለማዳን ተወልዶ፣ ተጠምቆና አስተምሮ መከራ መስቀል የተቀበለበትን ቅዱስ ቦታ ለመሳለምና ለመጎብኘት እንደ ዛሬው አማራጭ መጓጓዣ ሳይኖር ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን የጉዞ እንግልት የተረዳው ካህን፣ ንጉሥ፣ መሐንዲስ፣ ድንበርና ዘመን ተሻጋሪው ጠቢብ ቅዱስ ላሊበላ ሕዝቡ በጉዞ ምክንያት የሚፈጠርበትን ውጣ ውረድ፣ እንግልት፣ ችግር፣ ስቃይና ሞት ለማስቀረት ፈቃደ እግዚአብሔርን በመጠየቅ አምሳለ ኢየሩሳሌምን ሀገራችን ላይ አንጿል፡፡

የቅዱሱን አሻራ የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ ሀብትነት ባሻገር የኪነ-ሕንጻ ጥበቡን ለማድነቅ በርካታ የውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ በዓለም ቀዳሚ ከኾኑት መስሕቦች አንዱ ኾኖ ቀጥሏል።

እኛ በመጣንበት መንገድ በምናፈራቸው ካህናት፣ ዘመኑን መዋጀት እንደማይቻል ደጋግመው የሚናገሩት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በጥንቱ አካሔድ ብቻ በመጓዝ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያንን ማስቀጠል ከባድ ፈተና መኾኑን በመገንዘባቸው እንደቅዱስ ላሊበላ መፍትሄው ላይ አተኩረዋል፡፡ “ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትን ገንብተን በውስጣቸው የሚያገለግሉ ታላላቅ ሊቃውንትን ከምናጣ፣ ታላላቅ ሊቃውንት አፍርተን እንደ ጥንቱ በድንኳን ብንገለገል ይሻላል” በሚል ቁልፍ መልእክት የአብነት ትምህርት ቤት ፕሮጀክት ቀርጸው ተግባራዊ ያደረጉት ወደ ጵጵስና ማዕረግ ከመምጣታቸው በፊት መጋቤ ሐዲስ ወብሉይ መምህር አባ ሳሙኤል ገላነው ተብለው በሚጠሩበትና ተማሪና መምህር በነበሩበት የንስሐ ልጆቻቸውን በማስተባበር በ፳፻፱ (2009) ዓ.ም ነበር።

የአብነት ትምህርት ቤት ፕሮጀክቶቹ በዘመናዊ አደረጃጀት የተደራጁና ኹለገብ ተተኪ ሊቃውንትን ኮትኩቶ ለማፍራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች የተሟሉላቸው ናቸው፡፡ አንዱ ከሌላው የሚለይባቸው ልዩ ልዩ አዳዲስ እሳቤዎችንም ይዘዋል፡፡ ለአብነት የአስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈለገ አእምሮ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በውጭ ሀገርና በታላላቅ ከተሞች ተወልደው የሚያድጉ ልጆች የኢትዮጵያዊነትን እሴትና የገጠራማውን ማኅበረሰብ የአኗናር ዘይቤ ለወራትም ኾነ ለዓመታት ማጥናት እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ ተገንብቷል፡፡

በመቄት ወረዳ ሥራ ከጀመረው የአስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈለገ አእምሮ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በተጨማሪ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐሳብ አፍላቂነትና በሀገረ ስብከቱ አስተባባሪነት ፫፻ (300) ወንዶችንና ፻ (100) ሴቶችን ተቀብሎ ማስተማር የሚያስችለው የወልድያ ወይብላ ምሥራቀ ፀሐይ ቅድስት ማርያም አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታው እየተጠናቀቀ ነው። ዳውንት ወረዳ የጨረቃ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሰባቱ ድድቅ መታሰቢያ የቅኔ ጉባኤ ቤት መሬት ተቀብሎ በጊዜያዊ ማረፊያ ሥራ ጀምሯል። በዋድላ ወረዳ ደግሞ የዮሐንስ ገብላዊ መታሰቢያ የነጃ ቅዱስ ሚካኤል አዳሪ የቅኔ ጉባኤ ቤት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ የግንባታ ቅድመ ዝግጅት ላይ ነው። ብፁዕ አቡነ ኤርምያስም እነዚኽኑ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ በጥቅምት ፳፻፲፯ ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በምሥል የተደገፈ መረጃ አቅርበው ገለጻ አድርገዋል።

ብፁዕነታቸው ማስተማርና መመገብ ከማይለየው አባትነትና ሐዋርያዊ አገልገሎታቸው ባሻገር በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ፕሮጀክቶቹን ለማስተዋወቅ የሚደክሙት ዓላማው እስከ ምን ድረስ ነው? ፕሮጀክቶቹ ያሉበት ደረጃና ቋሚ የገቢ ማስገኛስ ታስቦበታልን? በሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት የሚገኘው ልዩ ትኩረት የሚያሻው፣ “የቅዱሱ ዐይንና ጆሮ” ምስጢርስ ምንድ ነው? የሚሉትንና ሌሎች ተዛማች ሐሳቦችን በቀጣይ ክፍል እናስቃኛችኋለን።
ሰላም!