ዐይንና ጆሮ የሚያሻው፣ የቅዱሱ ዐይንና ጆሮ (ክፍል ሦስት)
ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ/ም (የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ)
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ነገን ዛሬ ለመሥራት የሚያደርጉትን ጥረት፣ የነገዋን ቤተክርስቲያን ታሳቢ ያደረገ ሰው የመፍጠር እቅድና ተግባራዊ እንቅስቃሴን ባለፉት ኹለት ክፍሎች አቅርበናል፡፡ የዛሬውን እነሆ፤
አንጋፋው ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት እንደ ሌላው ጸጋ ኹሉ በመንፈሳዊ አባቶችም እድለኛ ነው። አንጋፋው ሐዋርያ አረጋዊ ሰይፍ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስና ጎልማሳው ሰይፍ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሐዋርያዊ ጉዟቸው ኹሉንም የልማት ሥራዎች በየፈርጃቸው ያጣመረ ነው። የጥንታዊቷን ሐዋርያዊቷን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ክብር የማስመለስ፣ ዘመኑን የዋጀ አሠራር የመዘርጋት መንፈሳዊ ቁጭቱና ወኔው ተመሳሳይ ነው። ሃይማኖታዊ አስተምህሮን ከራስ አገዝ ኢኮኖሚ ልማት ጋር ያጋማደ ነው። ይኽም ሌላ ምክንያት የለውም፤ ሁለቱም ብፁዓን አባቶች “ለኩሉ ዘሥጋ ወለኵላ ዘነፍስ።” የሚለውን በቃልም በተግባርም የሚተረጕሙ በመኾናቸው የተገኘ መልካም እድል ነው።
መጽሐፍ “በጎቹ ድምፁን ይሰሙታል፡፡” እንዲል ሕዝበ ክርስቲያኑ የአባቶቹን ድምፅ ይሰማል፡፡ “ምክር ሠናይት ለኩሉ ዘይገብራ፡፡” የሚለውን ቃል ይኖራል፡፡ የአባቶቹን ምክር ሰምቶ ይተገብራል፡፡ በአጠቃላይ አባቶቹን ይከተላል፡፡ ምክንያቱም ይኽ ሀገረ ስብከት ታድሎ ብፁዓን አባቶቹ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ከማኅበራዊ ኃላፊነት ጋር አጣጥሞ የመወጣት የአባትነት ጸጋ ከተቸራቸው መካከል ናቸውና፡፡
ለአብነት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ወደ ሀገረ ስብከቱ ተሹመው ከተመደቡበት ማግሥት ብዙም ሳይቆዩ ዓለም ዐቀፍ ችግር የኾነው የኮቪዲ 19 ወረርሽኝ፣ በመቀጠልም በሰላም እጦት ምክንያት የስደት ኑሮ ተጋላጭ ወገኖችና የሰላም እጦቱ የወለዳቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች በአካባቢው መፈጠርና መኖር ብፁዓን አባቶችን በብዙ መልኩ እረፍት ነሥቷል፡፡
ይኽም ኾኖ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በአንድ ጎን በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት ያሉ ክስተቶችን በሕዝቡ ላይ የሚያደርሱትን አደጋ በመቀነስ ማኅበራዊ ኃላፊነት በመወጣት፤ በሌላ ጎን በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በሀገረ ስብከቱ የተጀመሩ ልማቶችን በመጠንም በዓይነትም አጠናክሮና አስፋፍቶ በማስቀጠል ሐዋርያዊ ጉዞአቸውን ያለ እረፍት ከማስቀጠል አልተገቱም። ቅድስት ቤተክርስቲያኗን ማእከል ያደረገው የብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ምኞትና ፍላጎቶች በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በእጅጉ ተጠናክረውና ተስፋፍተው ቀጥለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ወደ ጵጵስና ማዕረግ ከመምጣታቸው በፊት መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ አባ ሳሙኤል (ቆሞስ) ተብለው ተማሪና መምህር በነበሩበት ወቅት ልጆቻቸውን በቋሚነት ያስተምሩ ነበር፡፡ ጣእመ ስብከታቸው፣ የቃለ እግዚአብሔር መግቦታቸው፣ አጠቃላይ የመንፈሳዊ ሕይወት እንክብካቤያቸው የንስሐ ልጆቻቸውን ልብ ገዛ፡፡ ልጆቹም የመንፈስ አባታቸው ወደ ሌላ አካባቢ በመዛወር እንዳይርቋቸው ካላቸው ፍላጎት በመነሳት የሚቆዩበትን የተለያየ ዘዴ ፈጥረው አማከሯቸው፡፡ ከመሠረታዊ ፍላጎታቸው መካከል የመኖሪያ ቤት ሊገዙላቸው ማሰባቸውንም ገለጹላቸው፡፡ እሳቸው ግን “ባለትዳሮች ልጅ ወልደው በማሳደግ ለቁም ነገር ያበቃሉ፤ እኔ ደግሞ በምናኔ ሕይወቴ ከእኔ የተሻሉ ቤተክርስቲያንን የሚረከቡ ሊቃውንት የሚወጡበት አንድ ትምህርት ቤት ብሠራ” የሚል ሕልም ስለነበራቸው ኹለንተናቸው ቅድስት ቤተክርስቲያን በመኾኗ ለትውልድ የሚሆን ሥራ እንሥራ በማለት ወደ ቤተክርስቲያኗ ልማት የገቡት ከዛሬ 12 ዓመታት በፊት ነበር፡፡
ሐሳባቸውም ወደ ፕሮጀክት አደገ፤ ልጆቻቸውንም በወንጌል ለልማት አስተሳሰረ፡፡ የገጠሯን ቤተክርስቲያን ማልማት ለከተማዋ አካባቢ ለሚገኙ ቤተመቅደሶች ምንጭ እንደማጎልበት እንደሚቆጠር ተረድተው ነበር። ኾኖም የትኛው አጥቢያ ላይ የሚገኘው ሕዝብና ሰበካ ጉባኤ ሐሳቡን በትክክል ይረዳልኝ ይኾን? የሚለው ጥያቄ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ይኹን እንጂ ገንዘብ ሳይባክን የታለመለት ዓላማ ላይ ለማዋል የሚታመን መዋቅርና ቦታ መቃኘት ተጀመረ፡፡ ቦታ ከማመቻቸት ባሻገር ድጋፍ በማድረግ ኀላፊነቱን የሚወጣ፤ በተፈለገው የአሠራር ሥልት መሠረት ሥሩ ብሎ በጎ ምላሽ የሚሰጥ አጥቢያ ተፈለገ፡፡
በወቅቱ ይኽን በጎ ሐሳብ የሚረዳ አካል ለማግኘት ተግባቦት አንዱና ቀዳሚው በር ነበር፡፡ ሕልማቸው አስፋ ገነተጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ እውን ኾነ፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በመንፈስ ልጆቻቸው አስተባባሪነት፣ በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ጸሎትና ቡራኬ እየታገዙ የሰውን የሐሳብ ዳገትና ቁልቁለት በወንጌል ዶዘር እያስተካከሉ ፕሮጀክቱ እውን ኾኖ ወደ ማዕርገ ጵጵስና መጡ።
የፕሮጀክቱ አድማስ፣ ዓላማ፣ ራእይና ግብ፣ ጥንታዊና ባሕላዊ የአብነት ትምህርት ቤት ጎጆዎችን ወደ ሰገነት በመቀየር ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ደቀመዛሙርቱ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚያባክኑት ጊዜ ለንባብና ለበለጠ መራቀቅ እንዲያውሉት ማድረግን ታሳቢ ያደረገ’ንጅ፡፡ ብፁዕነታቸው ከሩቅ አሳቢ ልጆቻቸው ጋር ደቀመዛሙርቱን ተክተው እየለመኑ፣ በሔዱበት ኹሉ ለልጆቼ ብለው አስተባብረው ለክብራቸው ሳይጨነቁ አልባሳት፣ ምግብና መጠለያ እያሟሉ የደቀመዛሙርቱን እንግልት መቀነስን፣ ከእሳቸው የተሻሉ ሰዎችን ለመፍጠርም “ሀ” ብለዋል ጉዟቸውን ተያይዘውታል።
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ወደ ሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ሲመጡ ገና ተማሪና መምህር ኾነው የጀመሩትን የተዋሕዶ ልጆችን የማስተባበርና የሙያ ዐሥራት የመጠቀም ልምድ ፕሮጀክት እየነደፉ ለምእመናን ግልፅ ማድረግ፣ የችግሩን አሳሳቢነት በማሳየት የመፍትሔ ሐሳብ ማመንጨትን አጠናክረው ቀጠሉበት፡፡ የብፁዕነታቸውን ራእይ የተረዱ የቅድስት ቤተክርስቲያኗ የቀጣይ ዘመን እጣፈንታ የገባቸው በጎ አድራጊዎች ትኩረታቸው የደቀመዛሙርት መኖሪያ ፕሮጀክትን ብቻ አይደለም፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎቱ በገንዘብ እጥረት እንዳይስተጓጎል ተቋማቱን በበጀት የሚደጉሙ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ጎን በጎን ተግባራዊ ማድረግ ጭምር እንጂ፡፡
በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ከነበረበት ወደ ኋላ ያለውን ሀገረ ስብከቱ መልሶ ለማቋቋምና የአብነት ት/ቤቶችን፣ ልዩ ልዩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመደገፍ የሚያስችል የገቢ ምንጭና ቋሚ ሀብት ለማፍራት የራስ አገዝ ልማትን ለማስፋፋት ቀደም ሲል ከተገነቡት የተለያዩ ሕንጻዎች በተጨማሪ በግዥና በሊዝ በተገኙ የከተማ ቦታዎች ላይ በሀገረ ስብከትና በወረዳዎች የተለያዩ ግንባታዎችና የሕንጻ ግዥዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ በጎ አድራጊ ወገኖች በለገሡት የገንዘብ፣ የሐሳብ፣ የሙያ፣ የጊዜና የጉልበት ድጋፍ ሀገረ ስብከታችን በደሴ ከተማ ቧንቧ ውሃ አካባቢ ሆቴል ታይምና ስፓ ተገዝቶ ገቢ ማመንጨት የጀመረ ሲኾን ከ60 በላይ ለሚኾኑ ዜጎችም የሥራ እድል ፈጥሯል።
በወልድያ ከተማም አዳጎ አካባቢ 850 ካሬ ላይ ያረፈ G+7 ኹለገብ አገልግሎት መስጫ ሕንጻ በጥራትና በፍጥነት በመገንባት ላይ ሲኾን ለግንባታ ፕሮጀክቱ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪና ሌሎች ማሽነሪዎችን አሟልቶ ከ760 በላይ ለሚኾኑ ሰዎች ጊዜአያዊ የሥራ እድል ፈጥሮ እየገሰገሰ ነው፡፡
እነዚኽ ኹለት የአገልግሎት መስጫ ሕንጻዎች ቀጣይ ወልድያ ከተማ ላይ ሊገነባ በሒደት ላይ ላለው ባለ5 ኮከብ ሆቴል ግንባታ ፕሮጀክትና ለሌሎች ተያያዥ ልማቶች መልካም እርሾ ይዘዋል፡፡ በራስ አቅም ዘመናዊ ሆቴል ማስተዳደርና በራስ አቅም ግዙፍ ሕንፃ መገንባት መቻሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ልምድን፣ ክህሎትን ማስታጠቅ ጀምሯል።
በነገራችን ላይ ስለልማት ስናወራ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች አልጋ ባልጋ የሚከወኑ ብቻ አይደሉም፡፡ በየወቅቱ የሚፈጠሩና በየመንገዱ የሚደቀኑ እንቅፋቶች ቀላል ባይኾኑም በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት እየታለፉ እንጂ፡፡
ለአብነት ብናነሣ ሀገረ ስብከቱ በሚያስገነባው ግንባታ የማቴሪያል አቅርቦት ገልባጭ መኪና ሲገዛ እንዴት ጳጳስ ገልባጭ መኪና ይገዛል? ግንባታውስ ለምን ለተቋራጭ አይሰጥም? የእነሱ ሥራ ጸሎት አይደለም እንዴ? የሚሉ አልጠፉም። እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ እነ ቅዱስ ላሊበላ ያልተገለጡላቸው አንዳንድ ሰዎች፥ የእንስሳት እርባታና ሌሎች ፕሮጀክቶች ሲጠናከሩ መነኵሴ ዳዊት ይደግማል እንጂ ነጋዴ ሊኾን ነው እንዴ? በማለት የጥላቻ ፍረጃ የሚሰጡ፣ አንድ አንዶችም “ወኢይጻ ዐቢይ ነገር እምአፉክሙ” የሚለውን ቃል በመተላለፍ በአባቶች ላይ ዘለፋና ጽርፈት የመሰንዘር እንዲኹም ስም የማጥፋት ሙከራዎቹ ቀላል አይደሉም፡፡
ቅዱስ ላሊበላ የወገኖቹን የጉዞ እንግልት ለማስቀረት የድርሻውን ለመወጣት ሲነሣ እግዚአብሔር ጅማሬው ጥራና፥ ፍጻሜው ደግሞ መሠረት ላይ የኾነ ልዩ ኪነ-ሕንፃን ለዓለም እንዲያበረክት ጥበቡን ሰጠው፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስም የከተማዋን ቤተክርስቲያን ለመታደግ የገጠር የአብነት ትምህርት ቤቶችን መታደግ ተገቢ መኾኑን በመረዳት ገጠርና ከተማን ማእከል ያደረጉ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የሊቃውንትን ፍልሰት፣ የደቀ መዛሙርትን ችግርና እንግልት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት “የእኔ መኖሪያ ቤት ቅድስት ቤተክርስቲያን ናት” በማለት የጀመሩትን ልማት እግዚአብሔር አጋዥ እየሰጣቸው አንጋፋውን ሀገረ ስብከት በአንጋፋነቱ ማስቀጠልን ተያይዘውታል፡፡ የቅዱስ ላሊበላም ኾነ የብፁዕነታቸው ዕይታ የትውልድን ቁስል ማከም ሳይኾን እንዳይቆስል ቀድሞ መንከባከብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለዚያም ነው ዐይንና ጆሮ የሚያሻው የቅዱሱ ዐይንና ጆሮ ያልነው፡፡
አንዳንዴ መልካም አሠራሮች የዬራሳቸው ተግዳሮትና መልካም እድሎች መዘንጋት የሌለባቸው፣ በአስተማሪነታቸው መቃኘት ያለባቸው ክስተቶች ይስተዋላሉ።
ለምሳሌ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በጎልማሳነት ሐዋርያዊ ጉዟቸው ወቅት ወደ አንድ አካባቢ በመሔድ ሰው በመልካሙ ነገር ኹሉ ጠንካራና ትጉ እንጂ ሰነፍ መኾን እንደሌለበት ያስተምራሉ፤ የተረዱትን መልካም ተሞክሮ ያጋራሉ። “… አንድ አንዱ ክፍለ-ዓለም ለም አፈር የለውም። ጥሩ የአየር ጠባይ የለውም። ዜጎቹ የለማ አእምሯቸውን ተጠቅመው ለም አፈር ተሸክመው ጭነው በውሰድ ምርት ያገኛል። የእኛ አፈሩ ለም ነው፤ አየር ጠባዩ ምቹ ነው። ትርንጎ፣ ሎሚ፣ ጌሾ፣ ብርቱካን ብቻ አይደለም፤ ፓፓያ … መትከል መቻል አለብን።” በማለት የፓፓያ ጥቅምና ፍራፍሬ ያስተዋውቃሉ። ያው ወቅቱ እንደ ዛሬው “እምብርቱ እንደ ተተኮሰ”[1] ሳይጠይቁት የሚቀባጥረው ማኅበራዊ ሚዲያ አልተፈበረከም ነበር እንጂ የአካባቢው ሰው “ምን ዓይነት መነኵሴ ናቸው? እንዴት ምናምንቴ አምጥተው ትከሉና ብሉ ይላሉ? የመነኵሴ ደንበሩ ጡሙ፤ ቍረቡ፤ ተፋቀሩ የሚለው ደንበር ይበቃቸው አልነበር? አየ ጊዜ? እንደው አቡኖቹም እንደ ዘመኑ ኾኑ!” በማለት ትምህርቱን ያገኘው ማኅበረሰብ ውስጥ ውስጡን ያማ፣ ያጉረመርም፣ በዝምታ ይቃወም ነበር።
ይኽንን የሀሜት ተቃውሞና ውስጣዊ ቅራኔ በሆዱ ይዞ ሳያምንበት መንፈስ ቅዱስ ያከበረውን የጳጳስን ቃል መንቀፍ ጥሩ አለመኾኑን ፊደል ባልቆጠረ ንጹሕ ኅሊናው የሚገነዘበው እና በማጉረምረም ፓፓያ የተከለው አርሶ አደር ከጊዜ በኋ ፓፓያው ተተክሎ፣ አድጎና አፍርቶ መብላት ሲጀምር ጉዳዩ “ጣእሙ ወታእምሩ።” ኾነና ሲጥመው “እንዴት ተሳስተን ኖሯል? ያ መነኵሴ እኮ ልዩ የኾነ የዛፍ ላይ ቅቤ አበላን።” ማለት መቻሉን ከብፁዕነታቸው አንደበት በተደጋጋሚ ይደመጣል።
ዛሬም እየተሠሩ ያሉ መልካም ሥራዎችን በዐይን ዐይቶ በማረጋገጥ እንጂ ባልተጨበጠ አሉባልታ በመጠለፍ ሳይኾን የብፁዓን አባቶችን ሩቅ ዕይታ ተጋርተን ለተግባራዊነቱ በጋራ መረባረብ ከእያንዳንዱ አማኝ ይጠበቃል።
በአጠቃላይ ሀገረ ስብከቱ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ትውልድን ታሳቢ ያደረገ፣ የትውልድን ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ቅድስት ቤተክርስቲያኗን ማእከል ያደረገ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የበለጠ እንዲስፋፋ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመርኩዞ መደገፍ ያስፈልጋል።
የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው በሙሉ ዐቅም ወደ ሥራ እንዲገቡና ከአገልግሎት ፕሮጀክት ዘርፍ ወደ ምርት ሰጭ ፕሮጀክት ዘርፍ አድማሱን በማስፋት የትናንቱን የአባቶቻችንን ዘመን ለመመለስ እንዲችል ዐይንና ጆሮ የሚያሻውን የሀገረ ስብከቱን ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት በየመክሊታችን እንደግፍ መልእክታችን ነው፡፡
ሰላም!
#መግለጫ
[1] እምብርቱ የተተኮሰ ማለት ሳያስተውል ጥቅምና ጉዳቱን ሳይመዝን ሳይጠየቅ በራሱ ዕውቀት ፍላጎትና ስሜት ብቻ ተመርኩዞ የሚያወራ እንደ ማለት ነው።
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ይወዳጁ ለሌሎችም ያጋሩ።
~ቴሌግራም፡ https://t.me/NWDnews
~ዩቲዩብ፡ https://youtube.com/c/NorthWolloDioceseMedia
~ድረገጽ፡ https://eotc-nw.org
~ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/EOTCNWD
~ቲክቶክ፡ https://www.tiktok.com/@eotc.north?_t=ZM-8ukkHRXMOYg&_r=1