ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ከአባታቸው ከአቶ ገላነው ማሬ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ያምሮት ንጋቴ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ልዩ ስሙ አስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጋቢት 5 ቀን 1966 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በብሕትውና ይኖሩ ከነበሩት ከመልአከ ጽጌ አባ ገብረእግዚአብሔር ካሳው እና በመቄት ወረዳ አንሳውሃ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ገላው እውኔ ከፊደል ገበታ እስከ መዝሙረ ዳዊት ያሉትን የንባብ ክፍሎችን በየስልታቸው እንዲሁም የውዳሴ ማርያምን ዜማ ተምረዋል በመቀጠልም በደቡብ ጎንደር የደብረ ፀሐይ ጨጨሆ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ከሆኑት ከሊቀ ጠበብት መሪጌታ በላይ ከበደ (የአሁኑ አባ ይባቤ) የመዝሙረ ዳዊትን ንባብ እና የውዳሴ ማርያም ዜማን በመከለስ መስተጋብዕንና አርባዕትን ተምረዋል፡፡ እንዲሁም የቅኔ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ነቅዐ ጥበብ ለመጀመሪያ ቅኔ ተቀኝተዋል በመቀጠልም ወደ ምዕራብ ጎጃም በመሄድ ጨጎዴ ሀና ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሺፈራው ቅኔ እስከ ሥላሴ ነግረዋል፡፡ በባህር ዳር ሽንብጥ ሚካኤል ገዳም ከየኔታ መንግስቱ በሙሉ ቤት ሁለተኛ ቅኔ ተቀኝተው በተጨማሪም በዚያው ሽንብጥ ሚካኤል ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ ለአራት ወር የሚሰጠውን ኮርስ ተከታትለዋል ወደ ሰሜን ጎንደር ደንቢያ በመሄድ ገንበራ ኢየሱስ ከየኔታ እንባቆም የአቋቋም ትምህርትን ጀምረው የቁስቋምንና የህዳር ሰባት ቅዱስ ጊዮርጊስን ክብረ በዓል እንደተማሩ ወደ ሰሜን ወሎ መቄት ወረዳ በመሄድ ደብረ ገነት ዋርካዬ ማርያም ከየኔታ ገብረመስቀል ዳምጤ የአቋቋም ትምህርታቸውን ተምረዋል፡ በቀጣይም ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በመሄድ በወልቂጤ ዞን ከሚገኘው ምሁር ገዳም ከመስተጋብዕ እስከ ሠለስት ያሉትን ትምህርት ጾመ ድጓ እና መዝገብ ቅዳሴ ተምረዋል፡፡

የከንባታ፣ ሀድያ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ ጥረት በጥቅምት ወር 1996 ዓ.ም ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመምጣት የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜን ተምረው በከፍተኛ ማዕረግ ሰኔ 14 ቀን 2000 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የትምህርት ዕድሉን በማግኘት በዚሁ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከመስከረም 2001 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 2006 ዓ.ም ድረስ የብሉያት መጻሕፍት ትርጓሜን ተምረው በማጠናቀቅ በከፍተኛ ማዕረግ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡

ከ1989 ዓ.ም መጋቢት ወር እስከ 1992 ዓ.ም ህዳር ወር በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ወሊሶ ሀገረ ስብከት በደብረ ኃይል ጨፎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመሪጌትነት ያገለገሉ ሲሆን መሪጌታ ወልደትንሳኤ ገላነው ተብለው ይታወቁ ነበር ከ1993 ዓ.ም ህዳር ወር እስከ 1996 ዓ.ም መስከረም ወር ድረስ በመሪጌትነት፣ በንባብ መምህርነት እና በቅዳሴ በምሁር ገዳም ሰፊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ እንዲሁም በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጁ ጥያቄ መሠረት ከጠቅላይ ቤተክህነት ፍቃድ አግኝተው ለዐሥራ አንድ ዓመታት የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን በተማሩበት ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በመሆን ከሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በርካታ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት አገልግለዋል፡፡

የክህነት አገልግሎትን በተመለከተ የካቲት 16 ቀን 1984 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የድቁና ማዕረግን በባህርዳር ከተማ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተቀብለዋል፡፡ ማዕረገ ምንኩስናን በምድረ ከብድ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ገዳም በብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ እጅ መጋቢት 5 ቀን 1994 ዓ.ም ተቀብለው አባ ሳሙኤል ገላነው ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ እንዲሁም በእኚሁ አባት ቅስናንና ቁምስናን በ1997 ዓ.ም በምሁር ኢየሱስ ገዳም ተቀብለዋል::
በነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም የጵጵስና ሢመትን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አንብሮተ ዕድ ተቀብለዋል፡፡ በአሁኑም ሰዓት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡