ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በመንበረ ጵጵስናቸው ከሀገረ ስብከቱ የሙያ ድጋፍ አገልግሎት ሕብረት የየክፍል ተጠሪዎች ጋር ምክክር ባደረጉበት ወቅት የዕውቀት አሥራት የማበርከት ጅምር በጎ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አባታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አባቶቻችን ያቆዩልን ስንዱ እመቤት የሆነች ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ እንዲትሆን በየሙያችሁ በማገዝ መዋቅሩን ማዘመን ይጠበቃል ብለዋል ብፁዕነታቸው።
ዓባይን ዓባይ ያሰኘው ገባሮቹ ናቸው ያሉት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር ጠንካራ ሊሆን የሚችለው ማኅበራት፣ ምሁራንና ምእመናን ከካህናት ጋር በቅንጅትና በመናበብ ሥንሠራ ነው ብለዋል።
የሙያ ድጋፍ አገልግሎት ኅብረቱም አቅማቸው በፈቀደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በእውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ለማገልገል ቃል ገብተዋል።
የሙያ ድጋፍ አገልግሎት ኅብረቱ የምህንድስና፣ የጤና፣ የሕግ፣ ሥራ አመራርና ምጣኔ ሀብት፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ኮምፒውተር ሳይንስ፣ ቱሪዝም ልማትና ቅርስ ጥበቃ፣ ጥናትና ምርምር፣ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም የሚዲያ ዘርፎችን ያካተተ ኮሚቴ በብፁዕነታቸው ተቋቁሞ ሀገረ ስብከቱን በሙያ እያገዘ ይገኛል።
የምክክር ጉባዔው ብፁዕነታቸው የቀጣይ የሥራ መመሪያ ሰጥተው በቃለ ምእዳንና ቡራኬ ተጠናቋል።