ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም
የላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት የቅዱስ ላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በማዕከልነት አቅፎ በሥሩ የሚያስተዳደርቸው 164 አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ 17 ውቅር፣ የዋሻ ውስጥ ኪነ ሕንጻ፣ የዋሻ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትና በርካታ መስህብነት ያላቸው ቅርሶች የሚገኙበት ወረዳ ነው።
የቀጠና ጽ/ቤቱ የተገነባው ከወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጽ/ቤት ቅዱስ ላሊበላ ከተማ በስተ ምሥራቅ ከ40 እስከ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት በአቡነ ዮሴፍ፣ እንጃፋትና ግራራይ ቀበሌዎች የሚገኙ ሃያ አራት አብያተ ክርስቲያናትን በቅርብ ለማገልገል እንዲያመች ታስቦ ነው።
የቦታው ርቀትና የተሟላ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ምክንያት ያለውን ችግር ለመቀነስ፣ ወረዳ ቤተ ክህነቱ በቅርበት ክትልል ለማድረግና አስተዳደራዊ አገልግሎት ለመስጠት፣ በቀጠናው ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ መሰባሰቢያ ማዕከል በአቅራቢያቸው እንዲኖራቸው ለማስቻል እንዲሁም በሦስቱ ቀበሌዎች በሚገኙ 24 አብያተ ክርስቲያናት የሚኖሩ የአብነት መምህራን፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሥልጠናዎችን ለመስጠት የቀጠና ጽ/ቤቱን መገንባት ያስፈለገበት ምክንያቶች መሆናቸውን ከግንባታ ኮሚቴው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አብያተ ክርስቲያናቱ ግዳን ወረዳ፤ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ብልባላ ቅዱስ ጊዮርጊስና በዋግ ኽምራ ዞን የጋዝጊብላ ወረዳ በከፊል፤ ጠልፈጢት፣ ኩልመስክ፣ የጥራሪ ወንዝና በአላማጣ ራያ ወረዳ የመረዋ ቀበሌና አካባቢዎች ጋር ይዋሰናሉ።አካባቢው የበርካታ ቅርስና ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ቢሆንም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ውጣ ውረድ የበዛበት ከመሆኑ በተጨማሪ ከቦታው ርቀት፣ ከመሠረተ ልማት አለመሟላትና ከተቋማት አለመጠናከር ጋር ተያይዞ ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ መንፈሳዊ አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ ቆይተዋል።
ይህን የአስተዳደር፣ የልማትና የመንፈሳዊ አገልግሎት ችግር ለማቃለል የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ገዳማትና ቅርስ ክፍል ኃላፊ አባ ኀይለገብርኤል ፍሥሓ የላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት (ከ፳፻፯ – ፳፻፱ ዓ.ም) ከወረዳው ቤተ ክህነት ሠራተኞችና በቀጠናው ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመመካከር ከእንጃፋት ቀበሌ አስተዳደር 1512 ካሬ ሜትር ቦታ በመቀበል ንዑስ (የቀጠና ጽ/ቤት) እና የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለማስገንባት መወሰናቸውን በእለቱ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
ነዋሪነታቸው በካናዳ ቶሮንቶ የሆነ የአካባቢው ተወላጅ በላስታ፣ በግዳን፣ በዋግ ኽምራ ልዩ ዞን ጋዝጊብላ ወረዳዎች ከ36 በላይ አብያተ ክርስቲያናትን ንሥሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር ያሠሩና ንዋየ ቅድሳት በመርዳት ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ የሚገኙት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታደሰ አጠና የንሥሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር ከአባ ኀይለገብርኤል ፍሥሓ፣ ከወረዳው ቤተ ክህነት ሠራተኞችና በቀጠናው ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመሆን በምእመናን የጋራ ትብብር የስብከተ ወንጌል አዳራሽና የቀጠና ጽ/ቤቱን መገንባት ተችሏል።
240 ካ.ሜ ላይ ያረፈውና ከሦስት ሚሊዮን አንድ መቶ ስልሳ ሽህ ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ፣ ጽ/ቤት፣ የሠራተኞችና አሠልጣኞች ማረፊያ ግንባታ ተጠናቅቆ ግንባታውን ያስተባበሩት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታደሰ አጠና ፣ አባ ኀይለገብርኤል ፍሥሓ ፣ የሀገረ ስብከቱ ተወካይ፣ የላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች፣ የቀጠናው አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ የወረዳውና የቀበሌው የመንግሥት ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ማክሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ተመርቋል።
የቀጠና ጽ/ቤቱን ማደራጀት፣ የአገልጋዮችን ማረፊያ ማሟላት፣ ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ፣ ለካህናት፣ ለሰንበት ተማሪዎችና ለሰበካ ጉባኤ አባላት ሥልጠናዎችን ማዘጋጀትና ማሠልጠን በቀጣይ ለመሥራት በዕቅድ ተይዘዋል።
ቦታውን በማመቻቸት በግንባታው ላይ በሙያ፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማትና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።