ስለ ሀገረ ስብከቱ
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በክልሉ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት አንዱ ሲሆን የዋግ ሕምራ ሀገረ ስብከትን ጨምሮ ራሱን ችሎ ጽ/ቤት ከፍቶ ከተዋቀረበት ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ለ33 ዓመታት ያህል አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል። በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ውስጥ 1482 አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 27 የአንድነት ገዳማት፣ 27 በሰበካ ጉባኤ የሚተዳደሩ ገዳማት፣ 465 አድባራት እና 963 የገጠር አብያተ hርስቲያናት ናቸው። ከነዚህም ውስጥ የጎብኝን ትኩረት የሚስቡ የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ 116 ውቅር፣ ፍልፍልና የዋሻ ውስጥ ኪነ-ሕንጻ አብያተ ክርስቲያናትና ታሪካዊ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡
ራእይ
ኹለንተናዊ ሰብእናው የተጠበቀ፣ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር የጠነከረ፣ በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጣዕመ ሕይወትን የተላበሰ፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት ዝግጁ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዝቶ ማየት፤
ተልእኮ
- የእግዚአብሔርን ቃል ለሰው ልጆች ኹሉ ማስተማርና ማዳረስ
- ሰውን በኸለንተናዊ ሰብእናው ማገልገልና ማዳን
- ሰውን ሁሉ በነገረ መለኮትና በነገረ ጥበብ ትምህርት በማልማት በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ሕይወቱ የተሻለ ኑሮ እንዲኖረው ማድረግ
- ጥራትና ብቃት፣ ፍትሐዊነትና እኩል ተደራሽነት ያለው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለሰው ኹሉ ማበርከት
- የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመተግበር ቤተ ክርስቲያንንና አገልጋዮቿን በኢኮኖሚ ማበልፀግ
- በቴክኖሎጂ የታገዘ አዋጭነቱ አስተማማኝ የሆነ ጠቅላላ የሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲረጋገጥ ማድረግ
- የሰው ልጆች ኹሉ እኩልነት፣ ሰላምና ፍትሕ፣ ፍቅርና ስምምነት እንዲጠበቅ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ
- የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሠራር ግልጽ፣ ለሁሉም ተደራሽና ችግር ፈቺ እንዲሆን ማድረግ
- አሳዳጊ ያጡ ሕፃናትን መንከባከብና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንን መርዳት
ዕሴቶች
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅሊናን የሚረታ፣ አእምሮን የሚመሥጥ፣ ከጥንተ ፍጥረት ተነሥቶ በዘመነ አበው በሕገ ልቡና፣ በዘመነ ብሉይ በሕገ ኦሪት ተራምዶ መዳረሻውን ሕገ ወንጌል ያደረገ ጥንታዊ ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ በያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ የታጀበ ሥርዐተ አምልኮ፣ በጽሑፍና በትውልድ ቅብብሎሽ የተወረሰ የረጅም ጊዜ ትውፊት ባህልና ታሪክ፤ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር የበለጸገ፣ እግዚአብሔርን የሚወድና የሚፈራ፣ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝና ምክረ ካህን የሚቀበል ከአንድ ሚልዮን 345 ሽህ 860 በላይ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ የክርስቲያን ማኅበረሰብ
- ለምጣኔ ሃብትና ለምንፈሳዊ ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ በውብ ሥነ ተፈጥሮ፣ በሥነ ጥበብና በኪነ ጥበብ፣ በታሪክና በቅርስ ሃብት የበለጸገ ሀገረ ስብከት
- የእግዚአብሔርን ቃል ከሃገር ውስጥ ባሻገር ለመላው ዓለም ማዳረስ የሚችሉ 35 ሽህ ያላነሱ ሊቃውንት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም ከሃምሳ አምስት ያላነሱ ገዳማት
- ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሀገረ ስብከት ብሎም እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ የተዋቀረ ጠንካራ መዋቅር ያለው ሀገረ ስብከት