ከላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ጽ/ቤት ቅዱስ ላሊበላ ከተማ በስተ ምሥራቅ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ017 ቀበሌ እንጃፋት ከተማ የሚገኘው የአፄ አምባ ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት በብፁዕ አቡነ ቄርሎስና በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሀገረ ስብከታችን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ በሀገረ ስብከቱ ልዑካን የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን በካናዳ ቶሮንቶ ነዋሪ የሆኑት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታደሰ የንሥሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር ከሰበካው ካህናትና ምእመናን ጋር ለመገንባት ዝግጅት በማድረግና በመወሰን የመሠረት ድንጋዩ እንዲቀመጥ ተደረጓል።
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የገዳማትና ቅርስ ክፍል ኀላፊ አባ ኀይለገብርኤል ፍሥሓ፣ የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር ክፍል ኀላፊ ሊቀ ትጉሃን አደባባይ ሰፊው፣ የላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ይሄይስ ተመስገን፣ የወረዳው ቤተ ክህነት የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች፣ የአፄ አምባ ቅዱስ ገብርኤል አገልጋይ ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት ማክሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ሥርዐተ ጸሎት በማድረስ የመሠረት ድንጋዩ ተቀምጧል።
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታደሰ በላስታ፣ በግዳን፣ በዋግ ኽምራ ልዩ ዞን ጋዝጊብላ ወረዳዎች ከ36 በላይ አብያተ ክርስቲያናትን ንሥሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር አሠርተው ንዋየ ቅድሳት በመርዳት ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡