ሀገረ ስብከቱ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለምእመናን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ነው። (ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ)

ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም (ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት) በበጎ አድራጊ ባለሞያዎች የተዘጋጀው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ድረገጽ በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ቡራኬ ትናንት ሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ሥራ ጀምሯል። ድረገጹ (https://eotc-nw.org ) የሀገረ ስብከቱን መሠረታዊ መረጃዎች፣ ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች እና ሌሎች ስልታዊ ይዘቶችን ለህዝበ ክርስቲያኑ ለማድረስ ታልሞ የተሠራ ነው።
ድረገጹ በአጥቢያ ዶት ኮም (atbiya.com) በነጻ ተዘጋጅቶ ለሀገረ ስብከቱ ተበርክቷል።

ቤተ ክርስቲያኗ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት የባለሞያዎች እገዛ ወሳኝ በመሆኑ በሌሎች መስኮችም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብፁዕነታቸው አጽንዖት ሰጥተው አባታዊ መመሪያ አስተላልተዋል።

የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ፍሥሐ ጌታነህ በበኩላቸው ሀገረ ስብከቱ የበርካታ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርሶች መገኛ ከመሆኑ ባሻገር በአንጋፋው ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ እና በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ አባታዊ መሪነት ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ የልማት ሥራዎች እየተስፋፉበት መሆኑን ገልፀዋል። ሀገረ ስብከቱ ያለውን ሀብት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ለማስተዋወቅና ለማልማት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ግብዓት ለማሟላትም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ባለሙያዎች ቤተ ክርስቲያኗን በእውቀታቸውና በሞያቸው እንዲያገለግሏት ሀገረ ስብከቱ የባለሞያዎች ኅብረት አቋቁሞ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።  ድረገጹን ያበለፀጉት ባለሞያዎች ከሀገር ውጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በቀጣይ በስልጠና እና በሌሎች ጉዳዮች ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት የእንጃፋት አፄ አምባ ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።

ከላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ጽ/ቤት ቅዱስ ላሊበላ ከተማ በስተ ምሥራቅ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ017 ቀበሌ እንጃፋት ከተማ የሚገኘው የአፄ አምባ ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት በብፁዕ አቡነ ቄርሎስና በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሀገረ ስብከታችን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ በሀገረ ስብከቱ ልዑካን የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

“ባለሙያዎች የዕውቀት አሥራት በማበርከት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያኗ አእምሯዊ አሻራችሁን አስቀምጡ” ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ (የክብር ዶ/ር)

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በመንበረ ጵጵስናቸው ከሀገረ ስብከቱ የሙያ ድጋፍ አገልግሎት ሕብረት የየክፍል ተጠሪዎች ጋር ምክክር ባደረጉበት ወቅት የዕውቀት አሥራት የማበርከት ጅምር በጎ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አባታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የላስታ ወረዳ ቤተ ክህነት ንዑስ (የቀጠና ጽ/ቤት) እና የስብከተ ወንጌል አዳራሽ አስገንብቶ አስመረቀ።

የቀጠና ጽ/ቤቱና የስብከተ ወንጌል አዳራሹ በአቡነ ዮሴፍ ፣ እንጃፋትና ግራራይ አካባቢ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡