ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ከአባታቸው ከአቶ ገላነው ማሬ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ያምሮት ንጋቴ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ልዩ ስሙ አስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጋቢት 5 ቀን 1966 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በብሕትውና ይኖሩ ከነበሩት ከመልአከ ጽጌ አባ ገብረእግዚአብሔር ካሳው እና በመቄት ወረዳ አንሳውሃ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ገላው እውኔ ከፊደል ገበታ እስከ መዝሙረ ዳዊት ያሉትን የንባብ ክፍሎችን በየስልታቸው እንዲሁም የውዳሴ ማርያምን ዜማ ተምረዋል በመቀጠልም በደቡብ ጎንደር የደብረ ፀሐይ ጨጨሆ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ከሆኑት ከሊቀ ጠበብት መሪጌታ በላይ ከበደ (የአሁኑ አባ ይባቤ) የመዝሙረ ዳዊትን ንባብ እና የውዳሴ ማርያም ዜማን በመከለስ መስተጋብዕንና አርባዕትን ተምረዋል፡፡ እንዲሁም የቅኔ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ነቅዐ ጥበብ ለመጀመሪያ ቅኔ ተቀኝተዋል በመቀጠልም ወደ ምዕራብ ጎጃም በመሄድ ጨጎዴ ሀና ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሺፈራው ቅኔ እስከ ሥላሴ ነግረዋል፡፡ በባህር ዳር ሽንብጥ ሚካኤል ገዳም ከየኔታ መንግስቱ በሙሉ ቤት ሁለተኛ ቅኔ ተቀኝተው በተጨማሪም በዚያው ሽንብጥ ሚካኤል ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ ለአራት ወር የሚሰጠውን ኮርስ ተከታትለዋል ወደ ሰሜን ጎንደር ደንቢያ በመሄድ ገንበራ ኢየሱስ ከየኔታ እንባቆም የአቋቋም ትምህርትን ጀምረው የቁስቋምንና የህዳር ሰባት ቅዱስ ጊዮርጊስን ክብረ በዓል እንደተማሩ ወደ ሰሜን ወሎ መቄት ወረዳ በመሄድ ደብረ ገነት ዋርካዬ ማርያም ከየኔታ ገብረመስቀል ዳምጤ የአቋቋም ትምህርታቸውን ተምረዋል፡ በቀጣይም ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በመሄድ በወልቂጤ ዞን ከሚገኘው ምሁር ገዳም ከመስተጋብዕ እስከ ሠለስት ያሉትን ትምህርት ጾመ ድጓ እና መዝገብ ቅዳሴ ተምረዋል፡፡

የከንባታ፣ ሀድያ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ ጥረት በጥቅምት ወር 1996 ዓ.ም ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመምጣት የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜን ተምረው በከፍተኛ ማዕረግ ሰኔ 14 ቀን 2000 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የትምህርት ዕድሉን በማግኘት በዚሁ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከመስከረም 2001 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 2006 ዓ.ም ድረስ የብሉያት መጻሕፍት ትርጓሜን ተምረው በማጠናቀቅ በከፍተኛ ማዕረግ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡

ከ1989 ዓ.ም መጋቢት ወር እስከ 1992 ዓ.ም ህዳር ወር በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ወሊሶ ሀገረ ስብከት በደብረ ኃይል ጨፎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመሪጌትነት ያገለገሉ ሲሆን መሪጌታ ወልደትንሳኤ ገላነው ተብለው ይታወቁ ነበር ከ1993 ዓ.ም ህዳር ወር እስከ 1996 ዓ.ም መስከረም ወር ድረስ በመሪጌትነት፣ በንባብ መምህርነት እና በቅዳሴ በምሁር ገዳም ሰፊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ እንዲሁም በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጁ ጥያቄ መሠረት ከጠቅላይ ቤተክህነት ፍቃድ አግኝተው ለዐሥራ አንድ ዓመታት የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን በተማሩበት ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በመሆን ከሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በርካታ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት አገልግለዋል፡፡

የክህነት አገልግሎትን በተመለከተ የካቲት 16 ቀን 1984 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የድቁና ማዕረግን በባህርዳር ከተማ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተቀብለዋል፡፡ ማዕረገ ምንኩስናን በምድረ ከብድ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ገዳም በብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ እጅ መጋቢት 5 ቀን 1994 ዓ.ም ተቀብለው አባ ሳሙኤል ገላነው ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ እንዲሁም በእኚሁ አባት ቅስናንና ቁምስናን በ1997 ዓ.ም በምሁር ኢየሱስ ገዳም ተቀብለዋል::
በነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም የጵጵስና ሢመትን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አንብሮተ ዕድ ተቀብለዋል፡፡ በአሁኑም ሰዓት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በወሎ ክፍለ ሀገር በአሁኑ አጠራር በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በመቅደላ ወረዳ በቅን አምባ መድኃኔዓለም አጥቢያ ሚያዝያ 23-1932 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

እድሜያአቸው ለትምህርት እንደደረሰ በዳውንት ወረዳ የቀይ ቅድስት ማርያም ቤተ ቤተ-ክርስቲያን ከፊደል እስከ ግብረ ሰሞን በመቀጠልም ውዳሴ ማርያም ዜማን፣ መስተገብዕ፣ አርባዕትና ክስተት አርአያም ሠለስት ተምረዋል፡፡

በተጫማሪም ቅኔን ከመሪጌታ ታደሰ ለመጀመሪያ ጊዜ በመማር በመቀጠልም የቅኔውን ሙያ በበለጠ ለማሻሻል በደላንታ ባባ ነአኩተለአብ ከተባለው ቦታ ቅኔን ለሁለተኛ ጊዜ ከነአገባቡ ጠንቅቀው ተምረዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ዜማን በብልባላ ጊርጊስ፣ ዜማን፣ ዝማሬ መዋስዕት ፣ ጾመ ድጓንና ምዕራፍን በጎንደር ቅድስት ማርያም በሚገባ አጠናቀው ተምረዋል፡፡ በተጨማሪም በጎንደር ተንሶየ ቅድስት ማርያም እና በወገራ ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ከ4 ዓመታት በላይ አቋቋምን ተምረው አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀው ወጥተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በ1966 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ አዲስ አበባ መንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል የሐዲሳት ትርጓሜ ትምህርት እና በደብረሊባኖስ የዳዊትን ትርጓሜ ጠንቅቀው ተምረዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በመማር እንዲሁም በማስተማር በርካታ ዓመታትን በወላይታ እና በዙሪያዉ በሚገኙ ወረዳዎች በመዘዋወር ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ሰንበት ት/ቤት በማደራጀት በስነ ጥበበ ትምህርት ያስተምሩ ነበር፡፡ በክረምት ወቅትም ለወጣቶች ኮርስ በመስጠት በርካታ ሰባኪያነ ወንጌል አፍርተዋል።

ድቁናን ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ምንኩስና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቅስና ከብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል። በኋላም ቁምስናን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ተቀብለዋል።

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1971 ድረስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤተ ክህነት በልዩ ጽ/ቤት፣ በሰበካ ጉባኤና በስብከተ ወንጌል መመሪያዎች አገልግለዋል፡፡

ከ1971 እስከ 1972 ዓ.ም የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም አንድነት ገዳምን በሰላምና በፍቅር እየመሩ ቆይተዋል፡፡

ብፁዕነታቸዉ የጵጵስና ሹመት እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸዉን በተለያዩ ሀገራት በተለያየ የሥራ ደረጃ አገልግለዋል፡፡

ከህፃንነታቸው ጀምሮ በትምህርት ቤት በኋላም ከደብረ ሊባኖስ እስከወላይታ ከሲዳሞ እስከ ሸዋ በሥራ አስኪያጅነትና በሰበካ ጉባኤ አመራርነት፣ በስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ በምስካየ ኅዙናንና ህፃናት ማሳደጊያ መምሪያ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች የሰጧቸውን አገልግሎቶች መነሻ በማድረግ ግንቦት 30 ቀን 1979 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ተብለው ሢመተ ጵጵስና ተቀብለዋል። ከህዳር ወር 1980 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
በሰሜን ወሎና ዋግኸምራ እስከገጠር በመዘዋወር በርካታ መንፈሳዊ፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ ልማት አስፋፍተዋል።

አብነት ት/ቤቶች

አብነት ትምህርት ቤቶች የቤተ ክርስቲያናችን የህልውናዋ እስትንፋሶች ናቸው፡፡

በሀገራችን የማዕከላዊ መንግሥት ምስረታ ጉልህ ሚና የነበራት ቤተ ክርስቲያናችን ፊደል ቀርጻ፣ ብራና ፍቃና ቀለም በጥብጣ ዜጎችን ያስተማረች ቀዳማዊ ትምህርት ሚኒስቴር እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

በብፁዕ_አቡነ_ኤርምያስ አስተባባሪነት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በወልድያ ምስራቀ ፀሐይ ወይብላ ማርያም እየተገነባ ያለው መንፈሳዊ አዳሪ ትምህርት ቤት፤ በአገልጋይ እጥረት የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱ፣ ምዕመናንን አስተምረው ለንስሐ የሚያበቁ፣ ቀድሰው የሚያቆርቡ ማህሌታውያን በዕውቀት የተሞሉ ካህናትን ለማፍራት እና የነገዋን ቤተክርስቲያን ለማስቀጠል ዘላቂ ዓላማ ይዞ እየተገነባ ይገኛል።

ይህ የአብነት ትምህርት ቤት በ 22 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7 ሺህ ካ.ሜ የቤተክርስቲያኗ ይዞታ እና የከተማ አስተዳደሩ 15 ሺህ ካሜ በመፍቀድ ለዚህም ለተነሺ ባለ ይዞታዎች ሀገረ ስብከቱ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ በመክፈል የግንባታ ሥራው እየተካሄደ ነው፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ በአንድ ጊዜ በኹሉም የጉባኤ ቤቶች 300 ወንድ እና 100 ሴት በጠቅላላ 400 ተማሪዎችን በመቀበል ሊቃውንትን የሚያፈራ ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤት

መግቢያ

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመሥራቿ በእግዚአብሔር ከተመሠረተች ጀምሮ ልጆቿን በተለያየ መንገድ ሰብስባ ከማስተማሯም በላይ ልጆቿ ያስተማረቻቸውን በተግባር እንዲፈጽሙ ስታደርግ ቆይታለች። ስታስተምርም ከመሥራቿ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕይወትን መሠረት በማድረግ ነው። ቀድሞ በዘመነ ኦሪት፣ ከዚያም በዘመነ ነቢያትና ነገሥት በኋላም በዘመነ ሐዲስ ልጆቿ እግዚአብሔርን እንዲያውቁና ርሱን በማክበር እየታዘዙ እንዲኖሩ አድርጋለች።
ቤተክርስቲያን ኵላዊትና ዓለም ዐቀፋዊት እንደመኾኗ መጠን አንዲት ናትና በየትኛውም ዓለም ያሉ የሰው ልጆች ኹሉ በየሚግባቡበት ቋንቋ እግዚአብሔርን ዐውቀው እንዲያመልኩት ሳታስተምር የኖረችበት ጊዜ የለም፤ ይኹን እንጂ ዓለሙ የርሷን ድምጽ አልሰማ ብሎ ከእግዚአብሔር ይልቅ በዲያብሎስ ክፉ ምኞት እየተመራ አእምሮውን አጥቶ እያበደ ይገኛል፤ የቤተክርስቲያንን ድምጽ የሰሙ ግን በእግዚአብሔር መዳፍ ተደግፈው በኅሊና ዕረፍት በደስታ ይኖራሉ፤ እየኖሩም ነው። ታዲያ ለዚኽ ኹሉ ጉዞዋ ልጆቿ ተባብረው በፈጣሪዋ በእግዚአብሔር ረድኤት ዛሬ ላይ ደርሳለች፤ ቤተክርስቲያን ዓለም ዐቀፋዊት እንደመኾኗ ስለ ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴ መጻፍም ኾነ መናገር የጊዜ ጉዳይ ኾኖ ስለሚገድበን ስለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ትንሽ እንጠቁምዎ!
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፥ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብለው ከሚያምኑ ከሕንድ፣ አርመን፣ ሶርያና ግብጽ አኀት ተብለው ከሚጠሩት አንዷ ናት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታዲያ በመግቢያችን እንደገለጽነው ልጆቿን ሰብስባ እያስተማረች ወደ መንግሥተ እግዚአብሔርም እንዲገቡ በተግባር እንዲፈጽሙ ማለትም በሥጋ ወደሙ እየታተሙ በጎ እገዛንም ለፍጥረት ኹሉ እንዲያደርጉ እያስደረገች ሲኾን በኢትዮጵያ በኹሉም ክልሎችና አካባቢዎች ልዩ ልዩ መዋቅሮችን በመዘርጋት አገልግሎቷን ለኹሉም ተደራሽ እያደረገች ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤት ትርጕም

ሰንበት የሚለው ቃል በእብራይስጡ “ማቆም፤ ሰርቶ ማረፍ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ እግዚአብሔር ስድስት ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን እንዳረፈ (ዘፍ2*2) እለተ ሰንበት በሥጋ አርፈን በመንፈስ የምንበረታበት (የዮሐ.ራዕይ 1*3) የእግዚአብሔርን ውለታ የምናስታውስበት (ዘጸ 20*10) መልካም በማድረግ የምንጠመድበት ዕለት ነው፡፡ (ማቴ 12*2)።
በዚኽ ዕለት የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበትና ውለታው የሚወሳበት ሥፍራ ሰንበት ት/ቤት ይባላል፡፡ በእረፍት ቀናቸው /በሰንበት/ መንፈሳዊ ትምህርት የሚማሩ በእግዚአብሔር ቤት እያደጉ ለዓለም ብርሃን የሚኾኑ የክርስቲያን ልጆች ደግሞ ሰንበት ተማሪዎች ይባላሉ፡፡

የሰንበት ት/ቤት ዓላማ

ሕፃናትን በምግባር ማሳደግ፤ ወጣቶችን በሃይማኖት ማጎልመስ እና የአባቶችን አደራ ተረክቦና ጠብቆ የሚያስረክብ ባለ ራዕይ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት ጥቅም

፩. ሰንበት ትምህርት ቤት ሃይማኖቱን ጠንቅቆ ያወቀ መልስ ያለው ትውልድ ይፈጥራል፡፡
፪. ለቤተ-ክርስቲያንና ለሃገር የውስጥ ጉልበት፤ የውጭ ውበት የሚኾኑ ምርጥ ዜጎችን ያሥገኛል፡፡
3. ለቤተ-ክርስቲያን ተልዕኮዋን የሚያሳኩ እጆች፤ ጠላቷን የሚረቱ ኃይሎች የሚኾኑ ባለ ራዕይ ወጣቶችን ይቀርጻል፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤት ክርስትናን በማስፋፋት ምንፍቅናን በመከላከል ዓለማ›ቀፋዊ እውቅና አለው፡፡ በሰንበት ት/ቤት ያደጉ ልጆች በሚሰማሩበት ሥፍራ የተሳካላቸውና በማኅበራዊ ሕይወት የተዋጣላቸው መሆናቸው ሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ መሆኗን ያረጋግጣል፡፡ ሰንበት ት/ቤት ሥራ አስለምዳና ጸባይ አርማ ወደ ስኬት ተራራ የምታወጣን ደግ እናትን ትመስላለች፡፡ አበው እንደሚሉት እሳት ያልነካው ሸክላና በሰንበት ት/ቤት ያልተማረ ወጣት አንድ ናቸው፡፡

የሰንበት ት/ቤት አመሠራረት

በብሉይ ኪዳን “ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም እረፉ” (ዘጸ 20*10) በተባለው አምላካዊ ቃል መሠረት የአይሁድ ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል በመስማትና ውለታውን በማሰብ ያከብሩት ነበር፡፡ በዓመትም ሦስት ጊዜ ልጆች ወደ አምልኮ ሥፍራ ይወሰዱ እንደነበር አሪት ዘጸአት 23*17 ያስረዳል፡፡ የነቢዩ ሳሙኤልን ታሪክ ስናስታውስ ደግሞ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ ያድጉ እንደነበር እንረዳለን፡፡ (1 ሳሙ.3*1)
በሐዲስ ኪዳን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው በመቅደሱ መገኘቱ የሃይማኖት ልጆቹ በእግዚአብሔር ፊት ማደግ እንዳለብን አብነት ነው፡፡ ሉቃ 2*46 በሚያስተምርበት ጊዜም ሕፃናትን ማቅረቡ (ሉቃ 18*16) ልጆቻችሁ በፊቴ ይመላለሳሉ፤ ከቤቴ በረከትን ጠግበው ተንኮል በሌለበት ቃሌ ይደጉ ማለቱ እንደኾነ እንረዳለን፡፡
የመጀመርያዎቹን ክርስቲያኖች ሕይወት ስንመለከት ልጆቻቸው አብረው ተጉዘው የክርስትናንም የፍቅር ማዕድ ተካፍለው የአባቶቻቸውንም ሃይማኖት ወርሰዋል፡፡ ክርስትናው እየሠፋ ሲሄድ መከራም እየበዛ ሲመጣ ልጆችን በክርስቲያናዊ ዓላማና በሰማያዊ ራዕይ ማሳደግ ስላስፈለገ በ 200 ዓ.ም ገደማ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤት ተመሠረተ፡፡
ዓለም አቀፋዊና ክርስቲያናዊ ከኾኑት የአንጾኪያና የእስክንድርያ ት/ቤቶች የሚወጡ ደቀ መዛሙርት ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር ተጠቃሾች እንደኾኑ ታሪክ ይናገራል፡፡
ሀቢብ ጊዮርጊስን የመሰሉ ግብፃዊያን ዲያቆናት ወጣቶችን በሰንበት ትምህርት ቤት በማሰልጠን የእስክንድርያን ቤተ-ክርስቲያን ከመናፍቃን አድነዋል÷ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የቤተ-ክርስቲያን የውስጥ ጉልበት፤ የውጭ ውበት በመኾን ዓላማዋን ያሳካሉና፡፡

ሰንበት ት/ቤት በኢትዮጵያ

ትውልዱ ወደ ዘመናዊ ትምህርት በማዘንበል ሃይማኖቱን ችላ እንዳይል በማሰብ አባቶቻችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን በማወቅ የሚያድግ፤ መልስ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ከ 1935-1940 ዓ/ም ባለው ጊዜ ሰንበት ት/ቤትን በአዲስ አበባ መሠረቱ፡፡ በጊዜውም “ተምሮ ማስተማር” በሚል መጠሪያ ይታወቅ ነበር፡፡ ቀጥሎም በ 1953 ዓ.ም መመሪያ ወጥቶለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ትእዛዝ በየአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያኑ ሰንበት ት/ቤት እንዲቋቋም የተደረገ ሲኾን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመን በቃለ ዓዋዲው የሰንበት ት/ቤት አወቃቀር መመሪያ ተካተተ፡፡

ምግባረ ሠናይ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ችግረኞችን ለመርዳት ምግባረ ሠናይ (የበጎ አድራጎት) ክፍል ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በማቋቋም በሰፊው ትሠራለች።

ምግባረ ሠናይ ምእመናንን፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማስተባበር ችግረኞች፣ ጧሪና ረዳት የሌላቸው ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በቤተ ክርስቲያን አካባቢ መጠለያና ምግብ እንዲያገኙ ማመቻቸት፤ ጤናቸውንም በመንከባከብ ችግረኞች መንፈሳዊና ሥጋዊ አኗኗራቸው የተሻለ እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የስነ ልቦና ጥገና የሚደረግበት ዘርፍ ነው። ወላጅ ወይም አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት ጊዜያዊና ዘላቂ ርዳታ የሚያገኙበትን መንገድም ያመቻቻል።

ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ወላጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት አጥተው አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትን ከተለያዩ ረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አሳድጎ ለቁም ነገር በማብቃት የእረዥም ጊዜ ልምድ አለው። ሀገረ ስብከቱ ገነት የሕፃናት መርጃ ማዕከልን በማቋቋም በርካታ ለችግር ተጋላጭ ሕፃናትን መታደግ ችሏል።

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ (የክብር ዶ/ር) ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው የሰላም እጦት (ጦርነት) ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን በቋሚነት ለመንከባከብና ለማሳደግ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል።

በማዕከሉ 20 ሕፃናትን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በገነት ሕፃናት መርጃ ማዕከል ውስጥ እንክብካቤ ከሚደረግላቸው በተጨማሪ 10 ሕፃናት ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር ሆነው እንዲያድጉ ወጭአቸው ይሸፈንላቸዋል።

ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ አስተባባሪነት ከበጎ አድራጊዎች በተገኘ ከ1 ሚሊዮን 420 ሽህ ብር በላይ ገንዘብ በጦርነቱ ምክንያት ቤትና ንብረታቸው የወደመባቸው በተለይም የእርሻ በሬዎቻቸው የታረዱባቸው አርሶ አደሮች እስካሁን ከ60 በላይ ለሚሆኑት አንዳንድ በሬና የዘር መግዣ ጥሬ ገንዘብ ተለግሷል።

የሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ የእለት ደራሽ ምግብ፣ ጥሬ ገንዘብና ቁሳቁስ ለበርካታ ችግረኞች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በጦርነቱ የወደሙ ሁለት የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም የሕክምና ቁሳቁስና መድኃኒት ድጋፍ ተደርጓል።

ከሀገረ ስብከቱ በተጨማሪ የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ አረጋዉያን መንከባከቢያ ማዕከል በርካታ ጧሪ የሌላቸውን ተቀብሎ እየተንከባከበ ይገኛል።

ቅዱሳት መካናት

ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በርካታ ማኅደረ ታሪክ ቅዱሳት መካናት መገኛ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ የኦሪት መስዋዕት ሲሰዋባቸው የነበሩ ታሪካዊና እድሜ ጠገብ አድባራት፣ ውቅር፣ ፍልፍልና የዋሻ ውስጥ ቤተ መቅደሶችም አሉ፡፡ በ12ኛው ክ/ዘመን በጻድቅወንጉስ ቅዱስ ላሊበላ የተፈለፈሉትን የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ጣሪያው ክፍት ሆኖ ዝናብ የማያስገባው አቡነ አሮን መንክራዊ፣ ይምርሐነ ክርስቶስና ሌሎችም መካናት የሚገኙበት የተቀደሰ አካባቢ ነው፡፡
ልመናን ታክ በማድረግ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሞክሮ ማዕከል የሆነው የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስን ጨምሮ 21 የአንድነትና 5 በቁሪት የሚተዳደሩ ገዳማት በዚሁ አንጋፋ ሀገረ ስብከት ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ ገዳማትም 1229 አበው መነኮሳትና 1124 እናቶች መነኮሳይያት በአጠቃላይ ከ2353 በላይ መናኞች ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው በበረሀ እየኖሩ ስለዓለም ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት እየጸለዩ የሚገኙበት ይኸው ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ነው፡፡

ስለ ሀገረ ስብከቱ

የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በክልሉ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት አንዱ ሲሆን የዋግ ሕምራ ሀገረ ስብከትን ጨምሮ ራሱን ችሎ ጽ/ቤት ከፍቶ ከተዋቀረበት ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ለ33 ዓመታት ያህል አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል። በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ውስጥ 1482 አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 27 የአንድነት ገዳማት፣ 27 በሰበካ ጉባኤ የሚተዳደሩ ገዳማት፣ 465 አድባራት እና 963 የገጠር አብያተ hርስቲያናት ናቸው። ከነዚህም ውስጥ የጎብኝን ትኩረት የሚስቡ የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ 116 ውቅር፣ ፍልፍልና የዋሻ ውስጥ ኪነ-ሕንጻ አብያተ ክርስቲያናትና ታሪካዊ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡

ራእይ

ኹለንተናዊ ሰብእናው የተጠበቀ፣ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር የጠነከረ፣ በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጣዕመ ሕይወትን የተላበሰ፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት ዝግጁ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዝቶ ማየት፤

ተልእኮ

  • የእግዚአብሔርን ቃል ለሰው ልጆች ኹሉ ማስተማርና ማዳረስ
  • ሰውን በኸለንተናዊ ሰብእናው ማገልገልና ማዳን
  • ሰውን ሁሉ በነገረ መለኮትና በነገረ ጥበብ ትምህርት በማልማት በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ሕይወቱ የተሻለ ኑሮ እንዲኖረው ማድረግ
  • ጥራትና ብቃት፣ ፍትሐዊነትና እኩል ተደራሽነት ያለው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለሰው ኹሉ ማበርከት
  • የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመተግበር ቤተ ክርስቲያንንና አገልጋዮቿን በኢኮኖሚ ማበልፀግ
  • በቴክኖሎጂ የታገዘ አዋጭነቱ አስተማማኝ የሆነ ጠቅላላ የሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲረጋገጥ ማድረግ
  • የሰው ልጆች ኹሉ እኩልነት፣ ሰላምና ፍትሕ፣ ፍቅርና ስምምነት እንዲጠበቅ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ
  • የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሠራር ግልጽ፣ ለሁሉም ተደራሽና ችግር ፈቺ እንዲሆን ማድረግ
  • አሳዳጊ ያጡ ሕፃናትን መንከባከብና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንን መርዳት

ዕሴቶች

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅሊናን የሚረታ፣ አእምሮን የሚመሥጥ፣ ከጥንተ ፍጥረት ተነሥቶ በዘመነ አበው በሕገ ልቡና፣ በዘመነ ብሉይ በሕገ ኦሪት ተራምዶ መዳረሻውን ሕገ ወንጌል ያደረገ ጥንታዊ ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ በያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ የታጀበ ሥርዐተ አምልኮ፣ በጽሑፍና በትውልድ ቅብብሎሽ የተወረሰ የረጅም ጊዜ ትውፊት ባህልና ታሪክ፤ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር የበለጸገ፣ እግዚአብሔርን የሚወድና የሚፈራ፣ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝና ምክረ ካህን የሚቀበል ከአንድ ሚልዮን 345 ሽህ 860 በላይ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ የክርስቲያን ማኅበረሰብ
  • ለምጣኔ ሃብትና ለምንፈሳዊ ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ በውብ ሥነ ተፈጥሮ፣ በሥነ ጥበብና በኪነ ጥበብ፣ በታሪክና በቅርስ ሃብት የበለጸገ ሀገረ ስብከት
  • የእግዚአብሔርን ቃል ከሃገር ውስጥ ባሻገር ለመላው ዓለም ማዳረስ የሚችሉ 35 ሽህ ያላነሱ ሊቃውንት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም ከሃምሳ አምስት ያላነሱ ገዳማት
  • ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሀገረ ስብከት ብሎም እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ የተዋቀረ ጠንካራ መዋቅር ያለው ሀገረ ስብከት